open

ከሳዑዲ አረቢያ የመጣው የአልጌፍ የኢንቨስትመንት ቡድን በከተማዋ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት እንዳለው ገለፀ፡፡

  Tuiste/ሚዲያ/ዜና/ቱሪዝም/ከሳዑዲ አረቢያ የመጣው የአልጌፍ የኢንቨስትመንት ቡድን በከተማዋ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት እንዳለው ገለፀ፡፡

ከሳዑዲ አረቢያ የመጣው የአልጌፍ የኢንቨስትመንት ቡድን በከተማዋ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት እንዳለው ገለፀ፡፡

 

(አዲስ አበባ፤ ከንቲባ ጽ/ቤት) በሼክ ሳልማን አልጌፍ የተመራ የሳዑዲ አረቢያ ኢንቨስትመንት ቡድን በአዲስ አበባ ኢንቨስት ለማድረግ ያለውን ፍላጎት አሳየ፡፡ የኢንቨስትመንት ቡድኑ በቱርክ፣ በኢንዶኔዥያ፣ በማሌዥያ እና በሳዑዲ አረቢያ በሪል ስቴት ዘርፍ የተሻለ ተሞክሮ ያለው መሆኑና በአፍሪካ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ለመሠማራት ማቀዱን ታህሳስ 21 ቀን 2009 ዓ.ም በከተማ አስተዳደሩ የካቢኔ አዳራሽ በነበረው ውይይት ወቅት አስታውቋል፡፡

በበርካታ ባለሐብቶች ቅንጅት የተቋቋመው የአልጌፍ ኢንቨስትመንት ቡድን ወደ አገራችን መምጣቱ፤ የሁለቱን አገራት የርስ በርስ ግንኙነት በማጠናከር እና ኢኮኖሚያዊ አቅምን በማሳደግ ረገድ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው እምነታቸው መሆኑን የልዑካን ቡድኑ መሪና የአልጌፍ ኢንቨስትመንት ሊቀመንበር ሼክ ሳልማን አልጌፍ  በውይይቱ ወቅት ተናግረዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ሠላማዊ አገር መሆን፣ የአየር ንብረቷ ምቹነትና የሕዝቦቿ እንግዳ ተቀባይነት እንዲሁም ጠንካራ ሰራተኛነት በአገሪቱ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት ያሳደረባቸው መሆኑን ሊቀመንበሩ ጨምረው አስረድተዋል፡፡

የኢንቨስትመንት ልዑካን ቡድን አባላቱን በከንቲባ ጽ/ቤት ካቢኔ አዳራሽ ተቀብለው ያነጋገሩት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው በበኩላቸው፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የፈጠረው ምቹ ሁኔታ፤ በርካታ የውጭ ባለሀብቶች ወደ ከተማዋ መጥተው መዋለ-ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ከፍተኛ መነሳሳት ማሳደሩን ገልፀው፤ የሳዑዲ አረቢያ ኢንቨስትመንት ልዑካን ቡድን አባላትም ወደ አገራችን በመምጣት በኢንቨስትመንት ለመሳተፍ ፍላጎት ማሳየታቸው የከተማዋን እድገት ለማፋጠን እንደሚያግዝ ጠቁመዋል፡፡

የልዑካን ቡድኑ አባላት በተለይም በማኒፋክቸሪንግና በኢንዱስትሪ ዘርፎች ቢሰማሩ ይበልጥ ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉና በሂደቱም ለበርካታ ወገኖች ሰፊ የሥራ እድል የሚፈጠር በመሆኑ ባለሀብቶቹ በማኒፋክቸሪንግና በኢንዱስትሪ ዘርፍ ቢሰማሩ የከተማ አስተዳደሩ ፍላጎት መሆኑን ምክትል ከንቲባው ገልፀዋል፡፡

የሳዑዲ አረቢያ የአንቨስትመንት ቡድን በአገራችን ለሚያደርገው ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ማስፈፀሚያ ከ3 አስከ 4 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚደርስ መዋለ-ንዋይ ለማፍሰስ ፍላጎት እንዳለው በውይይቱ ወቅት ተገልጿል ፡፡

 

Read 439 times Last modified on Dinsdag, 17 Januarie 2017 07:24