open

“አባይ ግድብ የሀገራችን የኃይል አቅርቦት ዋነኛ ምንጭ ብቻ ሳይሆን፤ ለሀገራዊው የምጣኔ ሃብት መዋቅር ሽግግሩ መሰረት ጭምር ነው”

  Tuiste/ሚዲያ/ዜና/ልዮ ልዮ/“አባይ ግድብ የሀገራችን የኃይል አቅርቦት ዋነኛ ምንጭ ብቻ ሳይሆን፤ ለሀገራዊው የምጣኔ ሃብት መዋቅር ሽግግሩ መሰረት ጭምር ነው”

“አባይ ግድብ የሀገራችን የኃይል አቅርቦት ዋነኛ ምንጭ ብቻ ሳይሆን፤ ለሀገራዊው የምጣኔ ሃብት መዋቅር ሽግግሩ መሰረት ጭምር ነው”

 

(አዲስ አበባ፣ ከንቲባ ጽ/ቤት) የአዲስ አበባ ከተማ አስተደደር የከንቲባ ጽ/ቤት አመራሮችና ሰራተኞች በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ወቅታዊ የግንባታ ሂደት እና ቀጣይ ድጋፍ አሰጣጥ ዙሪያ ታህሳስ 16 ቀን 2010 ዓ.ም ውይይት  አካሄዱ፡፡

 

የውይይት መድረኩን የመሩት የከንቲባ ጽ/ቤት የፕሬስና ህዝብ ግንኙነት ዴስክ ኃላፊና የህዳሴ ግድብ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ኢያሱ ሰሎሞን እንደገለፁት፤ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያዉያን የሀገራዊ መግባባትና የኩራት ምንጭ ከመሆኑም ባሻገር ግድቡ በተፋሰሱ ሀገራት የወደፊት ዕድገት ሂደት ውስጥ የራሱን ጉልህ አስተዋፅኦ የሚያበረክት፣ ለሀገራችንም ተጨማሪ የዲኘሎማሲያዊ ድሎችን በማስገኘት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች የመደራደር አቅሟን እንድታሳድግ ያስቻለ ሀገራዊ ፕሮጄክት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የውይይት መድረኩን በንግግር የከፈቱት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአዲስ አበባ ከተማ ህዝባዊ ተሣትፎ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ዘውዱ ገብረኪዳን በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ህዝቦች በገቡት ቃል መሰረት በአንድነት መንፈስና በተጠናከረ መልኩ ባደረጉት ርብርብ የግድቡን ግንባታ ከግማሽ በላይ ማድረሳቸውን ጠቅሰው በዚህ ሂደት ውስጥ የከንቲባ ጽ/ቤት ሠራተኞች በአራት ዙር ላደረጉት ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

 

“እንደጀመርን እንጨርሰዋለን” በሚል ህዝባዊ ቁርጠኝነት የተጋመሰውን የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ከዳር ለማድረስ የጽ/ቤቱ ሠራተኞች የጀመሩትን አኩሪ የልማት ተሳትፎ ይበልጥ በማጠናከር በአምስተኛው ዙር የቦንድ ግዢ ላይ በተሟላ መልኩ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

 

የአባይን ግድብ ታሪካዊ ዳራ እና ግንባታው የደረሰበትን ወቅታዊ ደረጃ እንዲሁም ሲጠናቀቅ የሚያስገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በዝርዝር የሚያሳይና የውይይት መነሻ ሰነድ በአዲስ አበባ ከተማ የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ፀጋዬ ሽምብር ያቀረበ ሲሆን የግድቡ ግንባታ 62 በመቶ መድረሱን እና ቀሪው 38 በመቶ ቴክኒካል ስራ ብቻ መሆኑን እንዲሁም የውሃ ሙሌት ሥራ መጀመሩን አመልተዋል፡፡

 

አባቶቻችን በአድዋው ጦርነት ወቅት ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ታጥቆ ሀገራችንን ለመውረር የመጣውን የፋሺስት ጣሊያን ጦር በማንበርከክ ለመላው አፍሪካና የዓለም ጥቁር ህዝቦች ኩራት የሆነውን ድል ማስገኘታቸውን ያወሱት አቶ ፀጋዬ የአሁኑ ትውልድም የቀደምት አባቶቹን አንፀባራቂ ድል በልማት በመድገም አባይን በመገደብ ከአድዋ የማይተናነስ ታሪክ እየሰራ መሆኑን አሳይተዋል፡፡

 

የጽ/ቤቱ ሠራተኞች ለአምስተኛ ዙር የቦንድ ግዢ የወር ደመወዛቸውን በዓመት ክፍያ ለማዋጣት የተስማሙ ሲሆን፤ አብዛኞቹ የጽ/ቤቱ አመራርና ሠራተኞችም ከነሐሴ ወር 2009 ዓ.ም ጀምሮ በማዋጣት ላይ እንደሚገኙ የጽ/ቤቱ ከፍተኛ የፋይናንስ ባለሙያ ወ/ሮ ኤልሳቤጥ ተፈራ ገልፀዋል፡፡

 

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ስድስት ዓመት የሆነው ሲሆን፣ የግንባታ ሥራው በተደረገለት የዲዛይን የማሻሻያ ቀደም ሲል ከታቀደው የ5,000 ሜጋ ዋት የኃይል አቅርቦት ወደ 6,450 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት መሸጋገሩ ይታወሳል፡፡

Read 744 times