open

የኢኮኖሚ ሽግግሩን እውን ለማድረግ ኢንዱስትሪ ትልቅ ሚና እንዳለዉ ተገለፀ

  Tuiste/ሚዲያ/ዜና/መሰረተ ልማት/የኢኮኖሚ ሽግግሩን እውን ለማድረግ ኢንዱስትሪ ትልቅ ሚና እንዳለዉ ተገለፀ

የኢኮኖሚ ሽግግሩን እውን ለማድረግ ኢንዱስትሪ ትልቅ ሚና እንዳለዉ ተገለፀ

 

(አዲስ አበባ፣ ከንቲባ ጽ/ቤት)፣ የአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ያዘጋጀው ስምንተኛው የቴክኒክና ሙያ ሳምንት፣ በተለያዩ መርሃ-ግብሮች ከየካቲት 26-30 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ በኢግዚቪሽን ማዕከል ተከብሯል፡፡

 

የቢሮው የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽንና የቴክኖሎጂ ሽግግር ዋና የስራ ሂደት መሪ አቶ በላይ ከፍያለው፣ ቴክኒክና ሙያ ተቋማት በዋናነት ሁለት ዓላማ አንግበው መቋቋማቸውን አስታውሰው፤ የመጀመሪያው መደበኛ እና አጫጭር ስልጠና መስጠት ሲሆን ሌላው ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማትን ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ የመስሪያ ቦታዎችን የስራ እንቅስቃሴ በመጎብኘት ድጋፍ ማድረግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

 

የኢንዱስትሪ ኤክስቴሽን ድጋፍ ማድረግ ኢንተርፕራይዞች ምርታማና በገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማስቻሉንና በአራቱ ፓኬጆች ማለትም የካይዘን ስራ ብክነትን በመቀነስ ምርታማነትን መጨመር፤ ክህሎትን መሙላት፣ የንግድ ስራ አያያዝ፣ የመዝገብ አያያዝ አዋጭ የሆነ ምርት አምርተው ገበያውን እንዲያዩ ማድረግና የቴክኖሎጂ ሽግግር በእስትራተጂው እንደተቀመጠው፤ እስከ 2017 ዓ.ም ቴክኖሎጂን የመቅዳት ስራን በማከናወን ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ ሽግግር ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

 

ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ ኤግዚብሽን ማድረግ መጀመሩን ያስታወሱት አቶ በላይ፣ ይህም የቴክኒክና ሙያ ውጤቶች፣ቴክኖሎጂዎችን ማሳየትና ማስተዋወቅ እንዳስቻላቸው ጠቁመዋል፡፡ ነፃ የፈጠራ ስራ ባለቤትነት ያላቸውን ቴክኖሎጂዎች በመቅዳት የቴክኖሎጂ ሽግግር ማድረግ እንደሚገባ የጠቆሙት ስራ ሂደት መሪው፤ በአሁኑ ሰዓት ከዩኒቨርሲቲ የወጡ ተማሪዎችም ወደ ቴክኒክና ሙያ ተቋማት በመምጣት፣ አጫጭር ስልጠናዎችን በመውሰድ የፈጠራ ባለቤቶች በመሆን ላይ እንደሚገኙና የዩንቨርስቲ የመግቢያ ውጤት ይዘውም በቴክኒክና ሙያ የመሰልጠን ፍላጎት ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ መምጣቱ፤ በዘርፉ ላይ እየተያዘ ያለውን አዎንታዊ ግንዛቤ የሚያመላክት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

 

የእንጦጦ ቴክኒክ ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ የኢንዱስትሪ ኤክስቴሽንና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ዲን አቶ አርአያ በላይ በበኩላቸው፤ በዚህ በስምንተኛው የቴክኒክና ሙያ ሳምንት በየኮሌጆቹ የተሰሩ ቴክኖሎጂዎችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ መደረጉን በመጠቆም፤ የዘንድሮዉ የቴክኒክና ሙያ ሳምንትን ከቀደሙት ለየት የሚያደርው፣ አንበሳ የከተማ አውቶብስ ድርጅት አገልግሎታቸውን ጨርሰው ያለምንም ስራ የቆሙ አስር አውቶብሶችን ለኮሌጁ ሰጥቶ፤ በፓይለት ደረጃ  አገልግሎት እንዲሰጡ የማድረግ ስራ መሰራቱ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

 

በዚህም የእንጦጦ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ አራቱን አውቶብሶች በመውሰድ  በውበት ሳሎንነት፣ በካፌና ሬስቶራንትነት፣ በሞባይል ጥገናና ሽያጭ እንዲሁም በአርት ጋለሪነት ጥቅም ላይ ለማዋል መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡ በቀጣይም ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮው ከአንበሳ የከተማ አውቶብስ ድርጅት ጋር በመነጋገር ከ7 መቶ በላይ አገልግሎት  የማይሰጡ አውቶብሶችን፣ የስራ ቦታና ስራ አጥ ወጣቶች በየክፍላተ- ከተማውና ወረዳዎች እንዲሰሩባቸው የሚደረግ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

 

በተያያዘም በኢግዚቪሽኑ ላይ ተሳታፊ የነበረው ሀይሌ ወንድሙ የግል ቅርፃ ቅርፅ ሰራተኛ ሲሆን በዚህ ኢግዚብሽን ለመነሻነት ጥሩ ልምድ እንዳገኘና በቀላሉ በራሱ ሞዴል የሚሰራውን የፈጠራ ሀሳብ ማግኘት መቻሉን ተናግሯል፡፡

 

በአዲስ አበባ 30 የመንግስት የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ሲኖሩ፤ ከነዚህ መካከል 6ቱ ፖሊ ቴክኒኮች፣8ቱ ኮሌጆች ሲሆኑ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችም አምስት ተቋማት፣ በግለሰቦች ደረጃ ደግሞ ከ3 መቶ በላይ የቴክኒክና ሙያ  ተቋማት ይገኛሉ፡፡ በነዚህ ተቋማትም በተያዘዉ የ2010 በጀት አመት በመንግስት ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ተቋማት 28 ሺህ አንድ ተማሪዎች፣በግል የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ተቋማትም 14 ሺህ 106 በድምሩ 1መቶ 42 ሺህ 107 ተማሪዎች በመደበኛ መርሃ ግብር ትምህርትና ስልጠናቸዉን በመከታተል ላይ ይገኛሉ፡፡

 

Read 601 times