open

Items filtered by date: Junie 2017

  Tuiste/ሚዲያ/ዜና/Items filtered by date: Junie 2017
Items filtered by date: Junie 2017

(አዲስ አበባ፣ ከንቲባ ጽ/ቤት)  የአዲስ አበባ የምግብ፣ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን ህገ- ወጥ የምግብና የመድኃኒት እንቅስቃሴን በመቆጣጠሩ ረገድ፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ሚያዚያ 4 ቀን 2009 ዓ.ም. በከተማ አስተዳደሩ ቲያትርና ባህል አዳራሽ አካሂዷል፡፡

ከአስሩም ክፍላተ - ከተሞች የመጡ የጤና ኤክስቴንሽን ሙያተኞች፣ ተቆጣጣሪዎችና አስተባባሪዎች ተሳታፊ በነበሩበት በዚህ መድረክ ላይ ተገኝተው መድረኩን በንግግር የከፈቱት የአዲስ አበባ የምግብ፣ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ወለቴ፣ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከከተማዋ የጤና ኤክስቴንሽን ሙያተኞች ጋር በመቀናጀት የህብረተሰቡን ጤና በመጠበቁ ረገድ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዋና ዳሬክተሩ አክለውም የህብረተሰቡን ጤና የሚጎዱ ምግብና መድኃኒቶች መኖራቸውንና ያገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸው ምግቦችና መድኃኒቶች ለገበያ እየቀረቡ እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡ ኃላፊነት የጎደላቸው ስግብግብ ነጋዴዎች ባዕድ ነገሮችን ከምግብ ጋር በመቀላቀል ለሽያጭ እንደሚያቀርቡም በማስታወስ፤ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ይህንንና መሰል ችግሮችን በመቆጣጠሩ ዙሪያ በተለይ ከጤና ኤክስቴንሽን ሙያተኞች ጋር በጋራ በመስራት ውጤት ሊያመጣ እንደሚችል እምነታቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡

Published in ማህበረሰብ

(አዲስ አበባ፣ ከንቲባ ጽ/ቤት)  በከተማ አስተዳደሩ የከንቲባ ጽ/ቤት ሠራተኞች የስትራተጂክ ዕቅድ ዝግጅት፣ ክትትል፣ ግምገማና ሪፖርት ዝግጅት ዳይሬክቶሬት፣ ከሥርዓተ-ፆታ የሥራ ክፍል ጋራ በጋራ ያዘጋጁት የኤች አይቪ ኤድስ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና፣ ግንቦት 28 ቀን 2009 ዓ.ም  በከተማ አስተዳደሩ አይሲቲ አዳራሽ ተካሒዷል፡፡

በዚህ ወቅት ከአዲስ አበባ ኤች አይቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠር ጽ/ቤት በአሰልጣኝነት የተገኙት አቶ መስፍን ሺበሺ እንደጠቆሙት፤  የሴክተር መስሪያ ቤት ሠራተኞች  ከኤች አይ ቪ ተጽዕኖ ነጻ የሆነ ህብረተሰብ በመፍጠር በጉዳዩ ላይ የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽዖ መወጣት ያለባቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የኤች አይ ቪ ኤድስ አመራር መቀዛቀዝ፣ የግብኣት ስርጭት ችግር መኖር፣ የሪፈራል ትስስሮሽ ችግር፣ ተጋላጮችን ኢላማ ያደረገ የምርመራ አገልግሎት አለመኖር፣ የፀረ-ኤች አይ ቪ መድሃኒት በተገቢው መልኩ ተደራሽ አለመሆንና የመሳሰሉት በሽታውን በመቆጣጠሩ ሒደት ዋንኛ ተግዳሮቶች መሆናቸውን አቶ መስፍን አስረድተዋል፡፡

እስካሁን የተገኙ ስኬቶችም በሽታውን ለማቆም ለሚደረገው ጥረት መደላድል እንጂ በስኬትነት ሊቆጠሩ እንደማይገባና ኢትዮጵያም እንደ ግብ በ2030 ኤች አይ ቪ ኤድስን የማስቆም እቅድ መያዝዋን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

Published in ልዮ ልዮ

በቹንቹን   ከተማ  የማህበራዊ  ጉዳይ  ቢሮ  ኃላፊ  ዮን - ገም- ዬዎን  የተመራ  የልዑካን  ቡድን  ግንቦት  7  ቀን 2009  ዓ.ም.  በአዲስ  አበባ ከተማ  አስተዳደር  ተገኝቶ  ውይይት  አካሂዷል፡፡

በዚህ  ወቅት  የከተማ  አስተዳደሩን  በመወከል  ልዑካኑን  የተቀበሉት  የአዲስ  አበባ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት  ቢሮ  ኃላፊ  አቶ  ፎኤኖ  ፎላ ፣ የሁለቱ  ከተሞች   እህትማማችነት  የጠነከረ  መሆኑን  በመጠቆም ፤ ለዚህ  ደግሞ  መሰረቱ  ኢትዮጵያዊያን  አባቶች  በቃኘው  ሻለቃ  አማካይነት  ከስልሳ  ስድስት  ዓመታት  በፊት  ለኮሪያ  ነፃነት  ያደረጉት  አስተዋጾኦ  እንደሆነ  አስታውሰዋል፡፡

የልዑካኑ  መሪ  ዮን - ገም - ዬዎን  በበኩላቸው፣  የሁለቱን  ከተሞች  ግንኙነት  የሚያጠናክሩ  በርካታ  ፕሮጀክቶች  መኖራቸውንና  በቆይታቸውም  ጉብኝቶች  ያሏቸው  መሆኑን  ተናግረዋል፡፡ መልዕክተኛዋ  ከከተማቸው  ከንቲባ  የተላከውን  5 ሺህ  ዶላር  ለቆሼ ተጎጂዎች  እንዲሰጥም  አበርክተዋል፡፡

የሚመለከታቸው የከተማዋ የሥራ ኃላፊዎች  በተገኙበት በዚህ  ውይይት  ላይ  የቹንቹን  ከተማ  ህፃናትና  ታዳጊ ወጣቶችን   በተመለከተ  በትምህርት  ቤትና ከዚያ  መልስ  ለተማሪዎቻቸው  የሚያደርጉላቸውን  ድጋፍና  ክትትል  በተመለከተ የልዑካን ቡድኑ ዓባል በሆኑት በኩዎን-ሃን-ና ገለፃ  ቀርቧል፡፡ በዚህም  በከተማዋ በተጠቀሰው እድሜ ክልል የሚገኙ ድጋፉ የሚደረግላቸው ተማሪዎች በእንግሊዝኛ  ቋንቋና በሒሳብ  ትምህርቶች  ላይ የማጠናከሪያ ትምህርት እንደሚሰጣቸውና  ደረጃውን  የጠበቀ  የቤተ - መፅሐፍት  አገልግሎቶችን ጭምር  እንደሚያገኙም  ተመልክቷል፡፡

Published in ቱሪዝም

(አዲስ አበባ፣ ከንቲባ ጽ/ቤት)የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤትና የአዲስ- ዙ ፓርክ አመራሮችና ሠራተኞች 26ኛውን ዓመት የግንቦት 20 የድል በዓል ግንቦት 19 ቀን 2009 ዓ.ም በከተማ አስተዳደሩ የምክር ቤት አዳራሽ በጋራ አክብረዋል፡፡

በመድረኩ ላይ ‹‹የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ስርዓት ባህሪያት፣ የዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባታ ሒደትና ስኬቶቹ ›› በሚል ርዕስ ሰነድ ቀርቦ፤ በበዓሉ ተሳታፊዎች ውይይት ተካሂዶበታል፡፡

በንጉሡም ሆነ በደርግ ሥርዓት ወቅት የነበሩት ሕገ-መንግስቶች፣ የኢትዮጵያን ሕዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ያረጋገጡ ባለመሆናቸው፤ የአገሪቱ የቁርጥ ቀን ልጆች ባደረጉት መራር ተጋድሎ፣ የኢትዮጵያን ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ አንድነትን ያረጋገጠ፤ ፌደራላዊ ስርዓት ሊፈጠር መቻሉ ተመልክቷል፡፡

በውይይቱ ወቅትም ከግንቦት 20 የድል ማግስት አንስቶ፤ መዲናችን አዲስ አበባን ጨምሮ በመላ አገሪቱ የተመዘገቡ የእድገት እምርታዎች መንገድ፣ ጤና፣ ትምህርትና ሌሎችም ወሳኝ የልማትና የእድገት ምህዋሮችን አስመልክቶ የደረሱበት ደረጃ ካለፈው ጋር በንጽጽር ቀርቧል፡፡

በዚህ ወቅት የበዓሉ ተሳታፊዎች እንደተናገሩት፣ ‹‹የዘንድሮውን የግንቦት 20 የድል በዓል ስናከብር፣ የተጀመረውን የጥልቅ ተሃድሶ ጉዞ በማጠናከር፤ በከተማዋ በአገልግሎት አሰጣጡ ሒደትና በሌሎቹም የሚስተዋሉ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከቶችና ብልሹ አሰራሮችን፣ በሕዝባዊ የዓላማ ጽናት ታግሎ ለማረምና ለማስተካል ከመቼውም ይልቅ ዝግጁነታችንን በማረጋገጥ ሊሆን ይገባል›› ሲሉ አስተያየቶቻቸውን ሰጥተዋል፡፡

ተሳታፊዎቹ አክለውም፣ አገሪቱ ቀደም ሲል ብዝሐነት የማይስተናገድባት፤ ማንነቶችና ቋንቋዎች የተዘነጉባት፤ እንደነበረችና ይህም እስከ ደርግ ስርዓት ውድቀት ድረስ የዘለቀ ጉዳይ መሆኑን፣ የጭቆናው ቀንበርም በከባድ መስዋዕትነት ተወግዶ፤ የዜጎች ዴሞክራሲያዊ አንድነት የቃል ኪዳን ሰነድ የሆነው ሕገ-መንግስት ከፀደቀ በኋላ እኩልነት፣ ልማትና ዘላቂ እድገት የተመዘገቡበት እንደሆነ ለዚህም የግንቦት 20 የድል በዓል መሰረት መሆኑን መረዳታቸውን ገልፀዋል፡፡

Published in ማህበረሰብ