open

Items filtered by date: April 2018

  Tuiste/ሚዲያ/ዜና/Items filtered by date: April 2018
Items filtered by date: April 2018

 

(አዲስ አበባ፣ ከንቲባ ጽ/ቤት) የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የህግና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የከንቲባ ጽ/ቤት በዘጠኝ ወራት ውስጥ ከዕቅድ አንፃር ያከናወናቸውን ስራዎች ሚያዝያ 5 ቀን 2010 ዓ.ም   በጽ/ቤቱ ስር ከሚገኙ ሁሉም ዳይሬክቶሬቶችና የስራ ክፍሎች የተውጣጡ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም ከአስሩም ክፍለ ከተሞች የቅሬታና አቤቱታ ማስተናገጃ ጽ/ቤቶች የመጡ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በተገኙበት በጽ/ቤቱ የICT አዳራሽ ግምገማውን አካሂዷል፡፡

 

በግምገማው የከንቲባ ጽ/ቤት የዘጠኝ ወር የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት በተጨማሪም የህዝብ ቅሬታ አቤቱታ ማስተናገጃ ጽ/ቤት የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት  በህዝብ ቅሬታ አቤቱታ ማስተናገጃ ጽ/ቤት ኃላፊ በአቶ ተክሌ ዲዶ ለቋሚ ኮሚቴው ቀርቧል፡፡

Published in ልዮ ልዮ

 

(አዲስ አበባ፣ ከንቲባ ጽ/ቤት) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እስከ መጭው ግንቦት ወር ድረስ ከድህነት ወለል በታች የሚገኙ 200 ሺህ የመዲናዋ ዜጎችን በስራ ዕድል ፈጠራና በምግብ ዋስትና ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ሚያዚያ 3 ቀን 2010 ዓ.ም  አስታውቋል።

 

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ድሪባ ኩማን ጨምሮ ሌሎች የከተማ አስተዳደሩ የስራ ኃላፊዎች፣ በሦስት ክፍለ-ከተሞች ማለትም በጉለሌ ወረዳ 7 ፣ በየካ ወረዳ 12  እና በአራዳ ክፍለ-ከተማ ወረዳ 1 በመሬት ተፋሰስ ልማትና በከተማ ግብርና ዘርፎች ዙሪያ የስራ እድል ተጠቃሚዎች እያከናወኗቸው የሚገኙ ተግባራትን ጎብኝተዋል።

 

ለአብነትም በጉለሌ ክፍለ ከተማ ከ14 ሺህ በላይ ዜጎች በመርሃ ግብሩ ተጠቃሚ ሲሆኑ፣ 2 ሺህ 399 የሚሆኑት በምግብ ዋስትና መርሃ ግብር የቀጥታ ተጠቃሚዎች እንደሆኑ ተጠቁሟል።12 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ በተለያዩ አምስት ዘርፎች ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡

 

በተመሳሳይም በየካ ክፍለ-ከተማ ጫካ ሚካዔል ተብሎ በሚጠራው ቦታ 21 ሄክታር መሬት ላይ 729 የሚሆኑ በተፋሰስ ልማት ላይ የተሰማሩ የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚዎች የስራ ክንውን ተጎብኝቷል። በአራዳም ልዩ ቦታው እሪ በከንቱ በሚባለው ቦታ በ0.12 ሄክታር ላይ 112 ወንዶችና 377 ሴቶች በድምሩ 489 የህብረተሰብ ክፍሎች በጓሮ አትክልት ልማት ላይ ተሳትፈው ገቢ በማግኘት ላይ እንደሚገኙ በጉብኝቱ ተመልክቷል፡፡

 

የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚዎች በተፈጠረላቸው የስራ እድል ደስተኞች መሆናቸውን ቢገልጹም፤ በስራቸው የሚያገኙት ክፍያ አነስተኛ መሆኑንና ከሚያገኟት አነስተኛ ብር ላይ ቁጠባ ቆጥበው የተደላደለ ኑሮ ለመኖር የሚያስችላቸው ባለመሆኑ የተሰማቸውን ቅሬታ ገልጸዋል።

Published in ማህበረሰብ

 

(አዲስ አበባ፣ከንቲባ ጽ/ቤት) የእቅድና በጀት ዝግጅት ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ባዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ላይ ከጽ/ቤቱ ልዩ ልዩ ዳይሬክቶሬቶችና የስራ ክፍሎች የተውጣጡ ከሰላሳ በላይ ሰልጣኞች ተካፍለውበታል፡፡

 

ስልጠናውን የሰጡት የእቅድና በጀት ዝግጅት ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተስፉ ውቤ አለሙ ሲሆኑ በስልጠናው በ2011 በጀት ዓመት የበጀት ፍላጎት ማቅረብ እና የ2011 በጀት ዓመት አመታዊ የበጀት አዘገጃጀትን አስመልክቶ የቀረቡ ይዘቶች ተካተውበታል፡፡

 

በቀረበው ሰነድም የበጀት ፍላጎት ማለት ወደፊት የሚሰራውን ወይም ይሳካል ተብሎ የሚታለመውን ዕቅድ ከግብ ለማድረስ በጀት አስፈላጊ በመሆኑ፤ በአግባቡ በማቀድና በመበጀት ለሚቀጥለው አመት የሚሰራው ስራ ምን ያህል በጀት ያስፈልገዋል ብሎ መወሰን ማለት እንደሆነ ተመልክቷል፡፡

Published in ልዮ ልዮ

 

(አዲስ አበባ፣ ከንቲባ ጽ/ቤት) ከንቲባ ድሪባ ኩማ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ መንግስት አምባሳደር ሚስተር ፍሬድሪክ ቦንተምስ የተመራውን የፈረንሳይ የመከላከያና ደህንነት ኮፕሬሽን ልዑካንን ሀሙስ ሚያዝያ 6 ቀን 2010 ዓ.ም  በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

 

ከውይይቱ በኋላም በፈረንሳይ ኤምባሲ በኩል በኢትዮጵያ የፈረንሳይ ኤምባሲ የመከላከያ አታሼ በኮሎኔል እስቴፈን ሪቾ እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር በኮማንደር አማኑኤል ረዳ ሐይሉ መካከል የፊርማ ሥነ-ስርዓት በከተማ አስተዳደሩ የካቢኔ አዳራሽ ተከናውኗል፡፡

 

የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስትና የፈረንሳይ ሪፐብሊክ መንግስት እረጅም እድሜ ያስቆጠረ የባህል፣ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ የግንኙነት ትስስር ያላቸው ሀገራት ሲሆኑ ይህንኑ የቆየ ወዳጅነት መነሻ በማድረግ፤ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለስልጣን አገልግሎት የሚያግዝ የቁሳቁስ ድጋፍ እና የሰው ሃይል ስልጠና ለመስጠት የታሰበ መሆኑ በፊርማው ስነ-ስርዓት ላይ ተገልጻል፡፡

Published in አስተዳደር

 

(አዲስ አበባ፣ ከንቲባ ጽ/ቤት) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት አመራሮችና ሰራተኞች፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠበትን ሰባተኛ ዓመት፣ መጋቢት 20 ቀን 2010 ዓ.ም በከተማው የምክር ቤት አባላት መሰብሰቢያ አዳራሽ በጥያቄና መልስ ውድድር አክብረዋል፡፡

 

በዕለቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የከንቲባ ጽ/ቤትና የካቢኔ ጉዳዮች ምክትል ኃላፊ አቶ ፀጋዬ አርዓያ፣ የህልውናችንና የኢኮኖሚያችን  መሠረት የሆነውን የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበትን ሰባተኛ ዓመት በዚህ ዓይነቱ የጥያቄና መልስ ውድድር ስናከብር፣ ‹‹እንዳገባደድነው እንጨርሰዋለን!›› የምንለው የጽ/ቤት ሰራተኞች ባደረጋችሁትና እያደረጋችሁት ባለው የገንዘብና የሞራል ድጋፍ ነው ብለው፤ ከተማ አስተዳደሩ ያዘጋጀው የቦንድ ሳምንት ላይ የተቻላችሁን አስተዋፆኦ አበርክቱ በማለት ፕሮግራሙን ከፍተዋል፡፡ 

 

ምክትል ኃላፊው አያይዘውም፣ ዘንድሮ ሰባተኛ ዓመቱን የሚያከብረውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ‹‹የማይቻል የሚመስለውን እሳት ችለን እንዳጋመስነው እንጨርሰዋለን›› በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ፕሮግራሞች እየተከበረ ሲሆን የጥያቄና መልስ ውድድር፣ የፎቶ ኢግዚቢሽን እንዲሁም በአዲስ አበባ ባህልና ቲአትር አዳራሽ በተዘጋጀ የሥዕል አውደ ርዕይና በቁንጅና ውድድር ጭምር በመከበር ላይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

Published in ልዮ ልዮ