open

ዜና

  Tuiste/ሚዲያ/ዜና

 

(አዲስ አበባ፣ ከንቲባ ጽ/ቤት) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እስከ መጭው ግንቦት ወር ድረስ ከድህነት ወለል በታች የሚገኙ 200 ሺህ የመዲናዋ ዜጎችን በስራ ዕድል ፈጠራና በምግብ ዋስትና ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ሚያዚያ 3 ቀን 2010 ዓ.ም  አስታውቋል።

 

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ድሪባ ኩማን ጨምሮ ሌሎች የከተማ አስተዳደሩ የስራ ኃላፊዎች፣ በሦስት ክፍለ-ከተሞች ማለትም በጉለሌ ወረዳ 7 ፣ በየካ ወረዳ 12  እና በአራዳ ክፍለ-ከተማ ወረዳ 1 በመሬት ተፋሰስ ልማትና በከተማ ግብርና ዘርፎች ዙሪያ የስራ እድል ተጠቃሚዎች እያከናወኗቸው የሚገኙ ተግባራትን ጎብኝተዋል።

 

ለአብነትም በጉለሌ ክፍለ ከተማ ከ14 ሺህ በላይ ዜጎች በመርሃ ግብሩ ተጠቃሚ ሲሆኑ፣ 2 ሺህ 399 የሚሆኑት በምግብ ዋስትና መርሃ ግብር የቀጥታ ተጠቃሚዎች እንደሆኑ ተጠቁሟል።12 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ በተለያዩ አምስት ዘርፎች ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡

 

በተመሳሳይም በየካ ክፍለ-ከተማ ጫካ ሚካዔል ተብሎ በሚጠራው ቦታ 21 ሄክታር መሬት ላይ 729 የሚሆኑ በተፋሰስ ልማት ላይ የተሰማሩ የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚዎች የስራ ክንውን ተጎብኝቷል። በአራዳም ልዩ ቦታው እሪ በከንቱ በሚባለው ቦታ በ0.12 ሄክታር ላይ 112 ወንዶችና 377 ሴቶች በድምሩ 489 የህብረተሰብ ክፍሎች በጓሮ አትክልት ልማት ላይ ተሳትፈው ገቢ በማግኘት ላይ እንደሚገኙ በጉብኝቱ ተመልክቷል፡፡

 

የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚዎች በተፈጠረላቸው የስራ እድል ደስተኞች መሆናቸውን ቢገልጹም፤ በስራቸው የሚያገኙት ክፍያ አነስተኛ መሆኑንና ከሚያገኟት አነስተኛ ብር ላይ ቁጠባ ቆጥበው የተደላደለ ኑሮ ለመኖር የሚያስችላቸው ባለመሆኑ የተሰማቸውን ቅሬታ ገልጸዋል።

 

(አዲስ አበባ፣ከንቲባ ጽ/ቤት) የእቅድና በጀት ዝግጅት ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ባዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ላይ ከጽ/ቤቱ ልዩ ልዩ ዳይሬክቶሬቶችና የስራ ክፍሎች የተውጣጡ ከሰላሳ በላይ ሰልጣኞች ተካፍለውበታል፡፡

 

ስልጠናውን የሰጡት የእቅድና በጀት ዝግጅት ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተስፉ ውቤ አለሙ ሲሆኑ በስልጠናው በ2011 በጀት ዓመት የበጀት ፍላጎት ማቅረብ እና የ2011 በጀት ዓመት አመታዊ የበጀት አዘገጃጀትን አስመልክቶ የቀረቡ ይዘቶች ተካተውበታል፡፡

 

በቀረበው ሰነድም የበጀት ፍላጎት ማለት ወደፊት የሚሰራውን ወይም ይሳካል ተብሎ የሚታለመውን ዕቅድ ከግብ ለማድረስ በጀት አስፈላጊ በመሆኑ፤ በአግባቡ በማቀድና በመበጀት ለሚቀጥለው አመት የሚሰራው ስራ ምን ያህል በጀት ያስፈልገዋል ብሎ መወሰን ማለት እንደሆነ ተመልክቷል፡፡