open

ዜና

  Tuiste/ሚዲያ/ዜና

 

(አዲስ አበባ፣ ከንቲባ ጽ/ቤት)፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው በቁጥር 6 የሚሆኑ የኮሪያ ልዑካንን ህዳር 7 ቀን 2010 ዓ.ም በልማት ዙሪያ በካቢኔ መሰብሰቢያ አዳራሽ አነጋግረዋል፡፡

 

ምክትል ከንቲባው ልዑካኑን እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት አዲስ አበባ ከኮሪያ ሁለት ከተሞች ማለትም ከሴኡልና ከቹንቹን ጋር የጠበቀ የእህትማማችነት ግንኙነት እንዳላት በመግለጽ፤ የደቡብ ኮሪያ የፓርላማ አባል የሆኑትንና የልዑካን ቡድኑን መሪ ሚስተር ቹንግ ባይጉንግ የዕለቱን አጀንዳ እንዲያቀርቡ ጋብዘዋቸዋል፡፡

 

ሚስተር ቹንግ ባይንጉንግም በበኩላቸው ስለተደረገላቸው አቀባበል አመስግነው ኢትዮጵያ  ሀገራቸውን ነፃ ለማውጣት ከዛሬ 67 አመታት በፊት ወታደሮቿን  ልካ ነፃ ማውጣቷንና ይህም የደቡብ ኮሪያ ዜጎች ካደረጉት ትግል የላቀ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡ በኮሪያ የርስ በርስ ጦርነት ወቅት በድህነት ውስጥ መሆናቸውን ተከትሎ፤  እርዳታ የሚቀበሉበት ጊዜ እንደነበርና በአሁኑ ወቅት ግን አደጉ ከተባሉት ሀገራት ተርታ መሰለፍ እንዲችሉ ብሎም በራሳቸው ፖሊስና ስትራቴጂ መመራት እንዲችሉ ኢትዮጵያ ያደረገችላቸውን እርዳታ  ማንም የኮሪያ ዜጋ ሊዘነጋው እንደማይችል አስረግጠው ተናግረዋል፡፡

 

የዕለቱን አጀንዳም ሲያቀርቡ ቹንቹን ከተማ በአዲስ አበባ ላይ የቡና ሙዝዬም፣ ፋብሪካና ሌሎች አዲስ አበባን ብሎም ሀገሪቱን ተጠቃሚና አገራቸው ከደረሰችበት የኢኮኖሚ ደረጃ እንድትደርስ የበኩላቸውን በመወጣትና ያለባቸውን ውለታ መክፈል ፍላጎት ያላቸው እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

‹‹እኛ የቡናና ሻይን እንዲሁም ገንዘብ ሚኒስቴርን አነጋግረን፣ ፕሮጀክታችንን ተቀብለውናል፤ አዲስ አበባም ይህንን ፕሮጀክት ተቀብላን ሥራውን በቅርብ ጊዜ መጀመር  እንፈልጋለን ብለዋል፡፡›› በፕሮጀክቱም ኢትዮጵያ በታሪክ  እንደሚታወቀው  የቡና መገኛ  ሀገር ሆና ሳለ ከቡና የምታገኘው ጥቅም ከዓለም ሀገራት እጅግ ዝቅተኛ የሆነ ገቢ መሆኑን ያስረዱት ሚስተር ቹንግ፤ ‹‹ እኛ የቡና ልማት  የለንም  ግን ከተለያዩ የዓለም  ሀገራት በማስገባት ትልቅ የውጭ ምንዘሬን ከቡና እናገኛለን፡፡ ስለሆነም ትክክለኛውን የቡና አዘገጃጀትና ባህሉን ጠብቆ ከዓለም ተወዳዳሪ የሆነ የቡና ሙዝዬምና ፋብሪካ መገንባት እንፈልጋለን›› ብለዋል፡፡ የዓለም ሀገራትን የሚያስንቀውን ኦርጅናል ቡና በማቅረብ ዓለም በሙሉ በአካል እየመጣ ኢትዮጵያን ብሎም አዲስ አበባን እንዲጎበኝና ከቱሪዝሙም ተጠቃሚ ለማድረግ ይህንን ፕሮጀክት ይዘው መምጣታቸውንም ጨምረው ተናግረዋል፡፡

 

(አዲስ አበባ፣ ከንቲባ ጽ/ቤት) ሁለተኛዉ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት  አምስተኛ ዓመት የስራ ዘመንና አንደኛ መደበኛ ጉባኤ ጥቅምት 30 ቀን 2010 ዓ.ም በከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት አዳራሽ ተካሂዷል፡፡

 

ምክር ቤቱ በጉባኤው ሁለት አጀንዳዎች ላይ ማለትም በ2010 በጀት ዓመት የመልካም አስተዳደር ዕቅድና የደሊቨሪ ዩኒት አሰራር ስርዓት ላይ ጥልቅ ውይይት አድርጓል፡፡ ፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮው የመልካም  አስተዳደር ችግርን በተለየ መልኩ አቅዶ ለምክር ቤቱ ሲያቀርብ ይህ የመጀመሪያው እንደሆነም ተገልጿል፡፡

 

በዕቅዱም በዋናነት በመሬት ልማት ማኔጅመንት ቢሮ 16፣ በንግድ ቢሮ ሰባት፣ በኢንዱስትሪ ቢሮና ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ሦስት፣ በኮንስትራክሽን ቢሮ 13፣ በቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ስድስት፣ በቁጠባ ቤቶች አራት፣ በቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ስድስት፣ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን 36፣ በአጠቃላይ በስምንቱ ቢሮዎች 91 ችግሮች ተካተውበታል ፡፡

 

በተጨማሪም በመንገዶችና ትራንስፖርት፣ በፍትህ፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በደንብ ማስከበር፣ በፖሊስ ኮሚሽን፣ በከተማ ነክ ፍርድ ቤቶች፣ በወሳኝ ኩነትና ምዝገባ፣ በምግብ መድሐኒትና ጤና እንክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን በተጨማሪም በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ቢሮዎች በአስሩም ክፍላተ - ከተሞች 1ሺህ አምስት መቶ ሃያ ሦስት፣ በ116 ወረዳዎች  1ሺህ ሁለት መቶ አርባ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ የለየ ሲሆን ችግሮቹንም ለመፍታት የመፍትሔ አቅጣጫዎችን እንዳስቀመጠላቸው ተመልክቷል፡፡