አዲስ አበባ ተብላ የተሠየመችው እቴጌ ጣይቱ ኅዳር ፲፬ ቀን ፲፰፻፸፱ ዓ/ም ፍልውሃ ፊል-ፊል ወደሚልበት መስክ ወርደው ሳሉ ከዚህ በፊት አይተዋት የማያውቋት አንዲት ልዩ አበባ አይተው ስለማረከቻቸው ቦታውን ‹‹አዲስ አበባ!›› አሉ ይባላል። አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ስትሆን በተጨማሪ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ እንዲሁም የብዙ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቅርንጫፎችና ሌሎችም የዓለም የዲፕሎማቲክ ልዑካን መሰብሰቢያ ከተማ ናት። ራስ-ገዝ አስተዳደር ስላላት የከተማና የክልል ማዕረግ ይዛ ትገኛለች። አብዛኞቹን የሀገሩ ቋንቋዎች የሚናገሩ ክርስቲያኖች እና ሙስሊሞች የሚኖሩባት ከተማ ናት። ከባሕር ጠለል በ2500 ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኘው ከተማ በግምት 2,757,729 ሕዝብ የሚኖርባት በመሆኗ የሀገሪቱ አንደኛ ትልቅ ከተማ ናት።

ከተማዋ እቴጌ ጣይቱ በመረጡት ቦታ ማለትም በፍል ውሐ አካባቢ ላይ በባላቸው በዳግማዊ ምኒልክ በ፲፰፻፸፰ ዓ.ም. ተቆረቆረች። የሕዝቧ ብዛት በያመቱ 8% (ስምንት በመቶ) እየጨመረ አሁን አራት ሚሊዮን እንደሚደርስ ይገመታል።

ከእንጦጦ ጋራ ግርጌ ያለችው መዲና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መገኛ ሆናለች። ይህም በመስራቹ የቀድሞው ንጉሠ ነገሥት ስም ቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ይባል ነበር።

አጼ ምኒልክ የሸዋ ንጉስ ሲሆኑ ደብረ እንጦጦ በደቡብ ዘመቻ ጊዜ ጠቃሚ ሆኖ ስላገኙት እዚያ ጥንታዊ የመንደር ፍርስራሽ በ1871 ዓ.ም. አይተው አንድ ያልተጨረሰ ውቅር ድንጋይ ቤተክርስቲያን ደግሞ በዚያ ጎበኙ። ይህ ቤተክርስቲያን ከግራኝ አሕመድ በፊት እንደ ቆመ አስረዳ።

ሚስታቸው እቴጌ ጣይቱ ቤተክርስቲያን በእንጦጦ ላይ በጀምሩበት ወቅት፣ የምኒሊክ ዝንባሌ ወደዚህ ስፍራ በተለይ ተሳበ፤ ሁለተኛም ቤተክርስቲያን ባቅራቢያው ሠሩ። ነገር ግን ማገዶም ሆነ ውኃ በማጣት አካባቢው መንደር ለመመሥረት አይመችም ነበር፤ ስለዚህ መስፈሪያው በውኑ የጀመረበት ከተራራው ትንሽ ወደ ደቡብ በሚገኘው ሸለቆ ውስጥ በ1878 ነበረ። በመጀመርያ ጣይቱ ፍልወሃ ምንጭ አጠገብ ለራሳቸው ቤት ሠሩ። ይህ ምንጭ ለቦታው ኦሮሞ ሕዝብ ፍንፍኔ ትብሎ ታወቀ፤ እዚህም እርሳቸውና የሸዋ ቤተመንግስት ወገን መታጠብ ይወዱ ነበር። ከዚያ በኋላ ሌሎች መኳንንቶች ከነቤተሰቦቻቸው አቅራቢያውን ሠፈሩ፤ ምኒልክም የሚስታቸውን ቤት ቤተመንግሥት እንዲሆን አስፋፉትና እስከ ዛሬ ድረስ ቤተ መንግሥት ሆኖ ቆይቷል። ምኒልክ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት በሆነበት ወቅት አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ሆነች። ከዚያ ጀምሮ ከተማዋ ዘልላ አደገች። ዛሬም በየመንገዱ ላይ ብዙ ባሕር ዛፎች የሚታዩበት ምክንያት አፄ ምኒልክ ስላስተከሏቸው ነው።

በ1928 ዓ.ም. በጦርነት ጊዜ የፋሺስቶች ሠራዊት ከተማዋን ወርረው ዋና ከተማቸውም አደረጉዋት፤ እስከ 1931 ድረስ የኢጣልያ ምስራቅ አፍሪቃ አገረ ገዥ ነበረባት። የኢጣልያ ሠራዊት በኢትዮጵያውያን አርበኞች ተደናቅፎ በእንግሊዝ ጭፍሮች ዕርዳታ በታላቅ ከተሸነፈ በኋላ፤ ዓፄ ኃይለ ሥላሴ በግንቦት 1933 ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ ይህም ቀን ከወጡ ልክ ከ5 አመቶች በኋላ ነበር። ወዲያው ከተማይቱ እንደገና ዋና ከተማቸው እንድትሆን መሠረታዊ ሥራ ጀመሩ።

በግንቦት 17 ቀን 1955 ዓ.ም. የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት (OAU) አስመሠረቱ፤ የድርጅቱም ጠቅላይ መስሪያ ቤት በአዲስ አበባ እንዲቆይ በመጋበዛቸው ሆነ። ይህ ድርጅት በ1994 ተፈትቶ በአፍሪካ ኅብረት ተተካ፤ ጠቅላይ መሥሪያ ቤቱ ደግሞ በአዲስ አበባ አለው። የተባበሩት መንግሥታት ምጣኔ ሀብት ጉባኤ ለአፍሪቃ (United Nations Economic Commission for Africa) ደግሞ ጠቅላይ መሥሪያ ቤት ባዲስ አበባ አለው። በ1957 ዓ.ም. አዲስ አበባ ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያን ስብሰባ ሥፍራው ነበረች።