በ1957 ዓ.ም “ሂሩት አባቷ ማን ነው?” በሚል ርዕስ የተዘጋጀው በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ባለጥቁርና ነጭ ፊልም ከ57 ዓመት በኋላ በዛሬው እለት በሸራተን አዲስ ለእይታ የበቃ ሲሆን በከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ አማካኝነት በይፋ ተመርቋል።
በምርቃቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ወ/ሮ አዳነች እንደተናገሩት ይህ ፊልም በኢትዮጵያ ታሪክ አዲስ ምእራፍ ከፋች ፊልም ብቻ ሳይሆን ከዚያ በኋላ ለመጡት የጥበብ ስራዎች ሁሉ መነሻ መሆን የቻለ ፤አይን የገለጠና በርካታ የጥበብ ሰዎች እንዲፈጠሩ ምክንያት የሆነ ታሪካዊ ስራ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያም ይህንን ሥራ የጀመረችው ከላይ በተጠቀሰው መልኩ ቀደም ብላ ቢሆንም በፊልሙ ኢንደስትሪ የሚፈለገውን ያህል ተጠቃሚ ሳትሆን ዛሬ ላይ ደርሳለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ የብዙ ባህሎችና ቋንቋዎች ፤እሴቶች አገር ስትሆን አሸባሪው ቡድን ይህንን አብሮነት ለማፍረስ ቢሞክርም እንዳልተሳካለት ገልፀዋል፡፡
በመሆኑም ኪነጥበብን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ገልፀው፤ የኪነጥበብ ስራዎቻችን የኢትዮጵያውያንን አብሮነትና አንድነት ፤የሚያጎላ ለሀገራችን የትንሳኤ ጉዞ የሚያግዝ ትልቅ አቅም መሆን አለበት በማለት ገልፀዋል፡፡
የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሀላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው በመክፈቻው እንደተናገሩት
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በእዳ ተይዞ የነበረውን ፊልም በጥንቃቄ ይዞ በማቆየት እና ለዚህ በማብቃቱ አመስግነው፤ አሁንም ለፊልሙ ኢንደስትሪው ብድሮች እንዲመቻች ጥሪ አቅርበዋል።
በስነስርዓቱ ላይ ይህ ስራ ለህዝብ እንዲደርስ አስተዋፅኦ ያበረከቱ የተለያዮ ባለሙያዎች ከከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እጅ እውቅና ተበርክቶላቸዋል።