የኮቪድ 19 ስርጭት በቅርብ ሳምንታት ጀምሮ በአዲስ አበባ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ሁኔታ እየተሰራጨ እና የሟቾችም ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ይገኛል ።
ከዚህ ጋር በተያያዘ በማህበረሰቡ ዘንድ የነበረው ጥንቃቄ መንገዶች እየቀነሱ ፤መዘናጋቶች የሚታዩ ሲሆን በተለይ ከክትባቱ ጋር በተያያዘ ማህበረሰቡ ዘንድ የተሳሳተ ግንዛቤ በመያዝ ከሚከተበው ሰው ቁጥር በሚፈለገው ደረጃ አይደለም።
በአዲስ አበባ በተከበረው የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ እና ነገ በቢሾፍቱ ከተማ በሚከበረው ሆራ አርሰዴ የኢሬቻ በዓል ህብረተሰቡ ከኮቪድ -19 ወረርሽኝ እንዳይጋለጥ አፍሪኸልዝ ኢቫንስ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሰት፤ ከአዲስ አበባ አስተዳድር ጤና ቢሮ ፤ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ዩኤስኤይድ ጋር በመተባበር በበዓላት ወቅት የሚኖረውን የወረርሽኝ መስፋፋት ለመቀነስ እና ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የግንዛቤ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛል።
በዛሬው ዕለትም የወረርሽኙን አስከፊነት የሚያሳስቡ መልእክቶችን በድምጽና በምስል (ቪዲዮ) አዲስ አበባ እና ቢሾፍቱ ከተማ ቀኑን ሙሉ በተለያዩ ተሸከርካሪዎች በመዞር የቅስቀሳ ስራ ይሰራል፡፡
በተጨማሪም ህብረተሰቡ የኮቪድ -19 ክትባት እንዲከተብና ጠቀሜታውን እንዲገነዘብ በድምጽና በምስል የታገዘ እንዲሁም በተለያዩ ስፍራዎች ላይ በተተከሉ ድንኳኖች አማካኝነት የጥንቃቄ መልእክት የሚተላለፍባቸው ልዩ የቅስቀሳ ፕሮግራሞች ተዘጋጅትዋል፡፡
በየትኛውም ቦታ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ ፣ በተደጋጋሚ እጅን በሳሙና በሚገባ መታጠቡን አልያም ሳኒታይዘር መጠቀሙን ብሎም ርቀቱን መጠበቁን መገንዘብ ይኖርበታል ።
ህብረተሰቡም የኮቪድ -19 የመከላከያ መንገዶችን ተግባራዊ ከማድረግ ጎን ለጎን በአቅራቢያው በሚገኝ ጤና ጣቢያ በመሄድ ነገ ዛሬ ሳይል የኮቪድ 19 ክትባትን በመውሰድ ራሱንና ቤተሰቡን ከሞት በመታደግ ኃላፊነቱን መወጣት ይገባል ።