የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መርሃ ግብሮች ያሰለጠናቸው 2039 ተማሪዎችን በዛሬው ዕለት አስመርቋል ።በምረቃው ስነስርዓት ላይ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አበቤ ፣የዩኒቨርስቲው የቦርድ ሰብሳቢ አባዱላ ገመዳን ጨምሮ ከፍተኛ አመራሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች ተገኝተዋልበ ምርቃት ስነስርዓቱ ላይ ለተማሪዎቹ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ያስተላለፉት ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በዩንቨርስቲ ቆይታችሁ ያሳለፋችኋቸው የደስታና የመከፋት ፤መውደቅና መነሳቶች ከመደበኛ ትምህርታችሁ ጎን ለጎን ችግርን የመጋፈጥ የህይወት ልምምድ ፣የመተሳስብ እና የመተባበር አቅም ያገኛችሁበት ሆኖ እንዳለፈ አምናለሁ ብለዋል ።የኮተቤ ሜትሮፓሊታን ዩኒቨርስቲን ጨምሮ የተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች በቀሰማችሁት የእውቀት ብርሃን በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ማንንም ሳይጠብቁ በመላው ኢትዮጵያ በሁሉም አቅጣጫ የሀገርን ሰላም በመጠበቅ እና በሀቀኝነት ህዝብን በማገልገል በተግባር መለወጥ እንደሚገባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል ።

ከተማዋ ለመማር፣ ለመኖር፣ ለመዝናናት፣ ለመታከም ተመራጭ እንድትሆን ለማድረግ በሚከናወነው የለውጥ ተግባራት ዩኒቨርስቲው የጀመረውን በጎ ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥል ወ/ሮ አዳነች አመላክተዋል ።የከተማ አስተዳደሩም ዩኒቨርስቲው ያለበትን የመሰረተ ልማት ችግር ፣ አደረጃጀቱን የማሻሻልና የማስፋፊያ ጥያቄን በአጭር ጊዜ ምላሽ እንደሚሰጥ እና እንደሚደግፍ ምክትል ከንቲባዋ ጠቁመዋል ።የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ብርሀነመስቀል ጠና በበኩላቸው ዩኒቨርስቲው በከተማዋ ቁልፍ የሆኑ ችግሮችን በጥናት እና ምርምር በመለየት የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል ።የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸው 1010 ሴቶች እና 1029 ወንዶች በጠቅላላው 2039 ተማሪዎችን ያስመረቀ ሲሆን በትምህርታቸው ከ3.5 በላይ ነጥብ ያስመዘገቡ ምሩቃን በከተማ አስተዳደሩ ስራ እንደሚመደቡ ቃል ተገብቷል ።