መሬት ወስደው ለበርካታ ዓመታት ሳያለሙ አጥረው ባስቀመጡ ተቋማትና ግለሰቦች ላይ ርምጃ መውሰዱን የአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማት ማኔጅመንት ቢሮ አስታወቀ፡፡
የቢሮው ኃላፊ ዶ/ር ቀንዓ ያደታ እንደገለጹት መሬት ከከተማ አስተዳደሩ ወስደው በሊዝ ዓዋጁ መሰረት ወደ ልማት ሳይገቡ ለዓመታት አጥረው ያስቀመጡ ተቋማትና ግለሰቦች መኖራቸው በተደረገው ማጣራት ተረጋግጧል፡፡
ቢሮው በሊዝ ዓዋጁ መሠረት ጊዜ ያለፈባቸው በመሆኑ ከተማ አስተዳደሩ 90 ሔክታር መሬቱን ተረክቦ በቅርቡ በሚወጣ ግልጽ ጨረታ ለዓለሚዎች ይተላለፋል ብለዋል፡፡
መሬት ተረክበው ግንባታ ጀምረው በማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ ያሉ ዓለሚዎች ደግሞ እስከ ሰኔ 30 ድረስ እንዲያጠናቅቁ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን ያወሱት ዶክተር ቀንዓ በቢሮው በኩል ጥብቅ ክትትል የሚደረግ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
የቢሮው ኃላፊ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ መሬት ውድ ሀብት በመሆኑ በቁጠባና በፍትሀዊነት አገልግሎት ላይ መዋል ይኖርበታል፤ ይሁን እንጂ የመሬት አስተዳደር ስራው በብዙ ችግሮች የተተበተበ በመሆኑ መፍትሄ የሚሻ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
መሬት ዋጋው ይጨምራል በሚል እሳቤ መሬት ከወሰዱ በኋላ ከማልማት ይልቅ አጥረው ለረጅም ጊዜ የሚያቆዩ ተቋማትና ግለሰቦች ከተማው ሊያገኝ የሚችለውን ኢኮኖሚዊ ጥቅም አሳጥተውታል ፡፡
ከመሬት ጋር የተያያዘው ችግር መንስዔዎችን ከተማ አስተዳደሩ በጥናት የለየ መሆኑንም የቢሮው ኃላፊ አክለው ገልጸዋል፡፡
የመሬት አስተዳደሩን ዘመናዊ ማድረግ አለመቻሉ ፣ ሌብነትና የመሬት ወረራ፣ ጠንካራ የፍትህ ስርዓት አለመኖር ሕዝቡን በዘርፉ የጸረ ሌብነት ትግል ላይ አለማሳተፍ እና ጠንካራ የድጋፍና ክትትል ስራ አለመሰራቱ ተጠቃሽ ችግሮች መሆናቸው ተገልጿል፡፡
ችግሮቹን ለመፍታት ይላሉ ዶክተር ቀንዓ በክብርት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የቅርብ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ ሲሆን የመሬት አስተዳደሩን በዘመናዊ መንገድ ለመምራት በካዳስተር የመመዝገብ ስራ መጀመሩን ገልጸዋል ፡፡
እንደ ዶክተር ቀንዓ ገለጻ በከተማው የሚገኙ ፓርሴሎችና የጋራ መኖሪያ ቤቶችን 25 በመቶ በካዳስተር መመዝገብ ተችሏል፤ ይህንን ስራ ማጠናቀቅ ሌብናትና ብልሹ አሰራርን ለማስተካከል እንደሚበጅም አብራርተዋል፡፡
ሌላው ወሳኝ ጉዳይ ተደርጎ የተገለጸው በጸረ ሌብነት ትግል ውስጥ ሕዝቡን በባለቤት የማሳተፍ አስፈላጊነት ነው፡፡ በተጨማሪም ከተማ አስተዳሩ በዘርፉ ተጠያቂነትን ለማስፈን እንደሚሰራ ዶክተር ቀንዓ ተናግረዋል፡፡