ከሁሉም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ የጽዳት ሰራተኞችን ለማመስገን እና ክብር ለመስጠት ልዩ የምስጋና መርሐግብር በወዳጅነት አደባባይ ተካሄደ ።በምስጋና መርሐግብር ላይ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እንደገለፁት የሌሊት ጭለማ ፣ ብርድ ፣ ዝናብ ፣ ፀሃይ እና መጥፎ ሽታ ሳይሉ ለከተማዋ ጽዳት ቀን ከሌሊት የሚተጉትን የጽዳት ሰራተኞች የከተማ አስተዳደሩ በእጅጉ ያመስግናቸዋል ብለዋል።አዲስ አበባችን ውብ እና ጽዱ ለማድረግ የሚለፉ ያልተዘመረላቸው ጀግኖችን ማመስገን እና ክብር መስጠት ከሁላችንም ይጠበቃል ያሉት ምክትል ከንቲባዋ የከተማ አስተዳደሩም ስራቸውን በማክበር ለጽዳት ባለሞያዎች ነጻ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲዘጋጅ መወሰኑንም አስታውቀዋል ።

የጽዳት ሰራተኞች 80 በመቶ እናቶች በመሆናቸው የገለጹት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የትራንስፖርት አገልግሎቱ ተጋላጭነታቸውን ይቀንሳል ብለዋል።የጽዳት ሰራተኞቹ ልፋታቸውን የሚመጥን ክብር እና ድጋፍ መስጠት ከሁሉም የሚጠበቅ በመሆኑ የሚደረግላቸው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ጠቁመዋል ።