በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሚገኙ ከፍተኛ አመራሮች፣ በክፍለ ከተማና በወረዳ ላሉ ኮር አመራሮች የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ “በመፍጠንና በመፍጠር የወል እውነቶችን ማፅናትና ቀጣይ የትግል ምዕራፋ” በሚል ርዕሰ ጉዳይ ባስቀመጣቸው አቅጣጫዎችና የቀጣይ ተልዕኮዎች ዙሪያ ሲሰጥ የነበረው የስልጠና መድረክ በዛሬው ዕለት ተጠናቋል።
የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የኢፌዴሪ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ፥ እያከናወንን ባለው የለውጥ ሂደት የወል እውነቶቻችንን በማጽናት ከውስጥም ከውጪም የሚደረጉ ጫናዎችን በጽናት በመሻገር በቀጠናው የታፈረችና የበለጸገች ሀገር ገንብተን ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ ከሁላችንም ይጠበቃል ሲሉ ተናግረዋል።
የመደመርን ጽንሰ ሀሳብ በአግባቡ ተረድተን ገቢራዊ ማድረግ ከቻልን በዓለም ላይ እየታዩ ያሉ አሁናዊ የፖለቲካ ሪዮተ-ዓለሞችን መደመር የማከምና የማረቅ ኃይል ያለው መሆኑን በመረዳትና ለሀገር ሁለንተናዊ ግንባታ አሻራችንን በአግባቡ ማኖር እንድንችል ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር መሆኑን አስረድተዋል ።
ሚንስትሯ አክለው ተሻግረው የሚመጡ ቀውሶችን በሚገባ ለማስተናገድ ተለዋዋጭ ዓለም አቀፍ ለውጦችን ያገናዘበ ዲፕሎማሲያዊ እና የፖለቲካ ትግል መከተል እንደሚያስፈልግ ገልጠው ጠንካራ ፓርቲ በመገንባት ጠንካራ ሀገረ መንግስት በመፍጠር ሂደት ውስጥ በሁለንተናዋ የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የከተማ አስተዳደሩ ብልፅግና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ በበኩላቸው የሀገራችንም ሆነ የከተማችንን ሁለንተናዊ ብልጽግና በሚፈለገው ደረጃና ፍጥነት ለማረጋገጥ ፓርቲው በሁሉም ረገድ አዳዲስ ሃሳቦችን ገቢራዊ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ በሁሉም ረገድ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ህዝባዊ አንድነትን ማጽናትና ኃላፊነት መሸከም የሚችል ጠንካራ ፓርቲ መገንባት ላይ ርብርብ ልናደርግ ይገባል ያሉት አቶ ሞገስ ከብልጽግና ፕሮግራም የሚመነጭ የሃሳብ አንድነትና ግልጸኝነት በአባሎች እና አመራሮቻች ዘንድ መፈጠር እንደሚገባና ከዚሁ በተጓዳኝ የላቀ ህዝባዊ ጠቀሜታ የሚኖራቸው ሰው ተኮር ተግባሮቻችን ላይ በዘላቂነት ተቀናጅተን ለእውነተኛና ተጨባጭ ለውጥ በአንድነት መስራት ከሁላችንም ይጠበቃልም ሲሉ አሳስበዋል ።
ለተከታታይ ቀናት ሲደረግ በነበረው ውይይት ላይ የተሳተፉ የከተማው አመራሮች የተናጠል እውነቶችን በመሻገር በከተማ ደረጃ የወል እውነቶችን ለመፍጠር በቅንጅት እንደሚሰሩ ገልጸው እያደገ ካለው የህዝብ ሁለንተናዊ የለውጥ ፍላጎት ጋር በተጓዳኝ “የመፍጠንና መፍጠር” አስፈላጊነት ላይ በዘላቂነት ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ አመላክተዋል ።