ሕወሃት በአገዛዝ ዘመኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ከፈጸማቸው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች መካከል በጋምቤላ ክልል በአኙዋክ ጎሳ አባላት ላይ የተፈጸመው ጭፍጨፋ ይጠቀሳል።
ሕወሃት ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት 424 የአኙዋክ ጎሳ አባላትን ጨፍጭፏል
ሕወሃት በአንባገነናዊ የአገዛዝ ዘመኑ 424 የአኙዋክ ጎሳ አባላትን ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ መጨፍጨፉን ትውልደ ኢትዮጵያዊው የአሜሪካ ኦስቲን ከተማ ምክር ቤት አባል ኦባላ ኦባላ ገለጸ።
ሕወሃት መራሹ አገዛዝ ኢትዮጵያ ውስጥ ከፈጸማቸው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች መካከል በጋምቤላ ክልል በአኙዋክ ጎሳ አባላት ላይ የተፈጸመው ጭፍጨፋ ይጠቀሳል።
በሚኒሶታ ግዛት የኦስቲን ከተማ ምክር ቤት አባል የሆነው ኦባላ በወቅቱ በጋምቤላ የተፈጸመውን ግድያ ለአለም አቀፍ ሚድያዎች ያብራራ ሲሆን እሱም ይህኑ ዘግናኝ ግድያ በመፍራት ከአገር ለመሰደድ መገደዱን አስታውቋል።
”በጋምቤላ 1995 ዓም (2003 በፈረንጆቹ)የተፈጸመው የዘር ማጥፋት በጎረቤት በደቡብ ሱዳን በኩል ከሌሎች የአኙዋክ ጎሳ አባላት ጋር ከአገር እንድሰደድ አስገድዶኛል”ሲል አስረድቷል።
በወቅቱ ሕወሃት መራሹ አገዛዝ በፈጸመው የዘር ማጥፋት 424 ሰዎች ሲገደሉ በርካቶች የሚኖሩበት መንደር ደግሞ እንዲወድም ሆኗል በማለት ገልጿል።
የምክር ቤት አባሉ ወደ አሜሪካ ከመምጣቱ በፊት ለ10 አመታት በስደተኞች ካምፕ ውስጥ መኖሩን ገልጾ፤ ካምፕ ውስጥ የነበረው ሕይወት ከባድ እንደነበረም አስታውሷል።
ትውልደ ኢትዮጵያዊው ኦባላ ኦባላ በቅርቡም ለአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ህወሓት በኢትዮጵያ በርካታ ዜጎችን ለከፋ ችግር መዳረጉን አብራርቶላቸው እንደነበር ይታወሳል።
ፕሬዚዳንት ጆ ባይደንን በአካል አግኝቶ ባነጋገረበት ወቅት እሱ በተወለደበት ጋምቤላ ከዚህ ቀደም ከሕወሃት መራሹ አገዛዝ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ተርፎ መውጣቱን ገልጾ ነበር።
ወጣቱ የምክር ቤት አባል ሕወሃት ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት የአኙዋክ ጎሳ አባላትን ጨምሮ መላው ኢትዮጵያውያን የኢ- ሰብዓዊ ድርጊቶች ሰለባ እንደነበሩ አስረድቷል።