የአ/አበባ ከተማ አስተዳደር በጀግንነት ለተሰዋው መቶ አለቃ ጌታቸው ሞረዳ ልጅ ህጻን ቢኒያም የመኖሪያ ቤት አስረከበ ::
ከንቲባ አዳነች አበቤ በህገወጥነት ተይዞ የነበረ ቤት ነው ለህጻን ቢኒያም አሰዳጊ ቤተሰቦች ያስረከቡት፡፡
የጌታቸው ሞረዳ ታሪክ የጀግንነት ጥግ ነው ያሉት አዳነች አበቤ በርካቶች ጀግንነትን ሰርተው ለሀገር ሉዓላዊነት ራሳቸውን መስዋዕት አድርገዋል ክብር ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
40 ቀን ሙሉ በትከሻው ተሸክሞ ሲፋለም የነበረው መቶ አለቃ ጌታቸው በዳግም ዘመቻ ወቅት መሰዋቱ ምን ያህል ለሃገር መሰጠት፤ ለአገር ዋጋ መክፈል እንደሆነ ያሳያል ሲሉም ገልጸውታል፡፡
ህጻን ቢኒያም በጀግንነት ማደግ ይገባዋል ያሉት ከንቲባ አዳነች መቶ አለቃ ጌታቸው ሞረዳ ለሀገሩ ባደረገው መስዋዕትንት ልክ በጀግንነት ተሰውቶ ትቶት የሄደውን ልጅ እኛ ተረክበን እናሳድገዋልን ብለዋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ ሁሌም ከህጻን ቢኒያም ጎን አይለይም በቀጣይም አዳሪ ትምህርት ቤት እንዲገባ ይመቻችለታል ብለዋል ከንቲባ አዳነች ፡፡
የከተማችን ነዋሪ ሆነው የዘመቱ የህጻን ቢኒያም አይነት የብዙዎች ታሪክ ስለሚኖር መረጃዎች እየተለዩ በተለያየ መንገድ ልጆቻቸው ኮርተው የሚያድጉበት መንገድ እንደሚመቻች ያላቸውን እምንት አነስተዋል። ተግባሩ በክልሎችም እንደሚተገበር አምናለሁ ብለዋል።
በአሁን ሰዓት የገጠመንን ጦርነት በአሸናፊነት በመወጣት አንገታችን ቀና እንዲል ላደረጉን ጀግኖች ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የቤቱ ዋጋው በከተማ አስተዳደሩ የሚሸፈን ሆኖ፤ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ፤ ጤና ቢሮ፤ ሳቢር አርጋው የአልሳም ባለቤት፤ ጊብሰን አካዳሚ የጤናና የትምህርት ቤት ወጪዎቹ ሙሉ እንደሚሸፍኑ ገልጸዋል፡፡