የሽብርተኞቹ የህወሃት እና የሸኔ ቡድን ተላላኪዎች ከውስጥ እና ከውጪ ድጋፍ በሚሰጧቸው ፀረ ሠላም ኃይሎች አማካይነት ከተማዋን ለማተራመስ የሚያደርጉትን ስውር እንቅስቃሴ ለማምከን እና ድብቅ ሴራቸውን ለማጋለጥ የአዲስ አበባ ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታ አካላት እና ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር ውጤታማ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ገልጿል፡፡
ፖሊስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መሰረት በማድረግ የሽብር ቡድኑን በመደገፍ በተጠረጠሩ ግለሰቦች መኖሪያ ቤት እያደረገ በሚገኘው ብርበራ እና ፍተሻ የተለያዩ ፈንጂዎች እኛ ሌሎች የጦር መሳሪያዎችም በተለያዩ ቦታዎች ተጥለው እና መሬት ውስጥ ተደብቀው ተገኝተዋል፡፡
በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የመሪ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ህዳር 3 ቀን 2014 ዓ/ም ከህዝብ በደረሰው ጥቆማ በወረዳ 13 ምስራቅ ሎቄ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በአንዲት ግለሰብ መኖሪያ ቤት ባደረገው ብርበራ መሬት ውስጥ ተቆፍረው በፌስታል ተጠቅልለው የተቀበሩ 2 ሽጉጦች ከ15 መሰል ጥይቶች ጋር፣ 70 ሺህ የኢትዮጵያ ብር፣ ሳንጃ እና የወርቅ እና የብር ጌጣጌጦች ከተደበቁበት ተቆፍረው እንዲወጡ ተደርጓል፡፡
የከተማችንን ፀጥታ ለማስጠበቅ ህብረተሰቡ በሙሉ ተነሳሽነት መረጃ እና ጥቆማ በመስጠት ለፀጥታ አካላት እያሳየ ለሚገኘው አጋርነት የአዲስ አበባ ፖሊስ ምስጋና አቅርቧል፡፡
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!