ከዚህ ቀደም ፖሊስ ያስተላለፈውን መልዕክት በመተላለፍ ርችት የተኮሱ ግለሰቦች ተይዘው በፍርድ ቤት በዋስ መለቀቃቸውን ፖሊስ ገልጿል።
በበዓላት ወቅት የሚተኮሱ ርችቶችን ሽፋን በማድረግ ሰላምን የማደፍረስ ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦች በሕገ-ወጥ መንገድ የገዙትን የጦር መሣሪያ እንደሚፈትሹ እና የተለያዩ የፀጥታ ስጋቶችን እንደሚፈጥሩ ፖሊስ ገልጿል።
የሕገ-ወጦቹን ድርጊት ለመከላከል እንዲቻል መስከረም 16 ቀን 2014 ዓ.ም በሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓልም ሆነ በልዩ ልዩ ምክንያቶች ማንኛውም ግለሰብም ሆነ ተቋም ከሚመለከተው አካል ፍቃድ ሳያገኝ ርችቶችን መተኮስ እንደማይችል ኅብረተሰቡ ተገንዝቦ ተገቢውን ትብብር እንዲያደርግም መልዕክቱን አስተላልፏል።
ጳጉሜ 5 ቀን 2013 ዓ.ም ለመስከረም 1 ቀን 2014 አጥቢያ ከለሊቱ 11 ሰዓት በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው ሩፋኤል ቤተክርስቲያን ውስጥ ሦስት ግለሰቦች የ2014 ዓ.ም አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ ርችት ሲተኩሱ ተይዘው ምርመራ ተጣርቶባቸው እያንዳንዳቸው በ4 ሺህ ብር ዋስ ተለቀው በፍርድ ቤት በመታየት ላይ የሚገኝ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውሷል።
በተመሳሳይ በቦሌ፣ በቂርቆስ እና በየካ ክፍለ ከተሞች ርችት ሲተኩሱ የተገኙ ግለሰቦች ጉዳይም በምርመራ ሂደት ላይ እንደሚኝም ፖሊስ ጨምሮ ገልጿል