የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከፍተኛ ክትትል እያስገነባቸው ከሚገኙና በቅርቡ ይጠናቀቃሉ ተብለው ከሚጠበቁ ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዱ የሆነው የትራፊክ ማኔጅመንት ህንፃ ግንባታ በመልካም የአፈፃፀም ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
በየካ ክፍለከተማ ወረዳ 08 በተለምዶ መገናኛ አካባቢ በ 7,50.75 ሜ.ስኩዌር ቦታ ላይ የሚያርፈውና ከምድር በታች 4 ወለሎች የሚኖሩት ይህ ህንፃ አሁን ላይ 85 በመቶ የፊዚካል አፈፃፀም ላይ ይገኛል፡፡
አሁን ላይ የፕሮጀክቱ ስትራክቸራል ስራ ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀ ሲሆን የጣሪያና የግድግዳ ሳር የማልበስ ስራ፣የአጥር ስራ፣የኤሌክትሪክ መስመሮች ገጠማ፣የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎች፣የኮርኒስ እንዲሁም የቀለም ቅብ ስራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡
ይህ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ በመዲናችን የሚስተዋለውን ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ለማሳለጥ ጉልህ ሚናን ከመጫወቱም ባለፈ የመንገድ፣የተሸከርካሪ እንዲሁም የእግረኛ ደህንነትን በማረጋገጥ ጤናማ የትራፊክ ፍሰት የሚስተዋልባት ከተማን ዕውን ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የህንፃው ሙሉ አካል ከምድር በታች የሚያርፍ ሲሆን 2,200 ሜ.ስኩዌር ቦታ የሚሸፍን የአረንጓዴ ስፍራ በህንፃው አናት ላይ ይኖረዋል፡፡