ክብርት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት እድሳት የምርቃት ስነስርዓት ላይ እንደተናገሩት ፤ዛሬ የምንመርቀው ህንጻ ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም ቅርስና ውድ ሃብት ነው ብለዋል፡፡
ስለሆነም እድሳቱ ጥንቃቄን ይፈልግ እንደነበረ ገልፀው በአንድ በኩል ታሪካዊ እሴቱንና ፋይዳውን በሌላ በኩል ጥራትና ምቾቱን መጠበቅ ያስፈልግ እንደነበር ገልፀው ለዚህ ነው ይህ ህንፃ ተገነባ እንጂ ታደሰ ማለት አይቻልም ብለዋል፡፡
እንዲሁም ይህ እድሳት በአገልጋዩ እና በተገልጋዩ መካከል የቤተሰብነት ስሜትን የሚፈጥር በአምስቱም ስሜት ህዋሳት የሚለካ ንፁህ፣ ምቹና አሰራርን የሚያዘምን ሆኖ ተጠናቋል በማለትም ገልፀውታል፡፡
ክብርት ከንቲባዋ በተጨማሪም እንደገለፁት ማስተካከል ማደስ የምንፈልገው ህንፃ ብቻ ሳይሆን አስተሳሰቦችንና አመለካከቶችን ጭምር ነው፤ ያሉ ሲሆን ያደስነው ለህዝባችን ያለንን አክብሮትና ፍቅር ነው ያደስነው በቢሮክራሲ የተተበተበን አገልግሎትም ነው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ከንቲባዋ እንዳሉት የከተማዋን ዲፕሎማቲክ መዳረሻነቷን ነጥቆ ለመውሰድ የተደረገው ጥረት መክኖ የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤን ለማስተናገድ በምንዘጋጅበት ወቅት የተመረቀ በመሆኑ ለኛ ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል፡፡
በመጨረሻም በግንባታው ሂደት የተሳተፉ አካላትን ሁሉ ያመሰገኑ ሲሆን በተለይም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ይህ ስራ ዲዛይን ከማስደረግ ጊዜ አንስቶ ለሁላችንም አርአያ በሆነ መንገድ የማያቋርጥ ክትትል ድጋፍ እና የሁልጊዜም አብሮነት ሳይለየን ፤እንዲህ ያማረ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ላበረከቱት የማይተካ አስተዋፅኦ በታላቅ አክብሮት ምስጋናችዉን አቅርበዋል ::
የአዲስ አበባ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ደቦ ቱንካ እንዲሁ በምረቃው ስነስርዓት ላይ እንደተናገሩት ከመስቀል አደባባይ እና ከአብርሆት ቤተመፅሃፍት ቀጥሎ የተመረቀ ሶስተኛው የሜጋ ፕሮጀክቶች አካል ነው ብለዋል፡፡
ጥንታዊነቱን እና ዘመናዊነትን አጣቅሶ በተለይም ከጎኑ ከሚሰራው አድዋ 00 ፕሮጀክት ጋር ተናቦ የተሰራ መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ ለዚህ አስደናቂ እድሳት እውን መሆን የላቀ አስተዋፅ ላበረከቱ አካላት እውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡