የስራ ኢንተርፕራይዝ እና ኢንደስትሪ ልማት ቢሮ በ11ኛ ጊዜ 169 ኢንተርፕራይዞችን ወደ መካከለኛ ኢንደስትሪ አሸጋገረ!!
የኢንተርፕራይዞች ሽግግር ለኢንደስትሪ መሰረት በሚል መሪ ቃል የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግርን ለማረጋገጥ በሚሰራው ስራ በዛሬው እለት የአዲስ አበባ ከተማ የስራ ኢንተርፕራይዝና ኢንደስትሪ ልማት ቢሮ በ11ኛ ዙር 169 ኢንተርፕራይዞችን ወደ መካከለኛ ኢንደስትሪ ማሸጋሩን ይፋ አድርጓል፡፡
በስነስርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እንደተናገሩት የሃገራችን የለውጥ ጉዞ ያልተዋጠላቸው ወገኖች ጉዟችንን ለማደናቀፍ ብዙ ስራዎችን ቢሰሩም ማንም ሊያስቆመው የማይችለውን የለውጥ ጉዞ ቀጥለናል በማለት አብስረዋል፡፡
አዲስ አበባም ነዋሪዎቿን የሃገራዊ ለውጥ ተጠቃሚ ለማድረግ ርብርብ እያደረገች ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች የሃገራችንን እድገት መሸከም የሚችልና የውጪ ጫናን መቋቋም የሚያስችል ሰፊ የስራ እድል መፍጠር ፤ስራ አጥነትንና ድህነትን የሚቀንስ፤ ቴክኖሎጂንና ፈጠራን የሚያበረታታ ኢንዱስትሪ ማስፋት ስራ እየተሰራ መሆኑን አውስተው ጥቃቅንና አነስተኛም ኢንዱስትሪው መሰረት መሆኑን ገልፀዋል፡፡
መንግስትም ከመስርያ ቦታ ከብድርና ሌሎች ድጋፎች ውጪ ዋናው ጉዳይ የኢንተርፕራይዞቹ ጥረትና ትጋት መሆኑን ገልፀው ምርትና ምርታማነታቸውን በማጠናከር ተኪ ምርቶችን በማምረት አገር እንዲያግዙ አደራ ብለዋል፡፡ጥረትና ትጋት ሁልጊዜም አሸናፊዎች ናቸው ሲሉም ገልፀዋል፡፡
ሃላፊነት ተጣለባቸው አካላትም ለኢንተርፕራይዞቹ ቢሮክራሲን በመቀነስ አገራዊ አቅም እንዲሆኑ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አድርገዋል፡፡
ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ለማካሄድ የኢንደስትሪ እድገትን ማበረታታ እንደሚያስፈልግ የገለፁት አዲስ አበባ ም/ከንቲባና የስራ ኢንተርፕራይዝና ኢንደስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ከታች ከጥቃቅን በመነሳት ጤናማ የሆነ የገበያ ስርዓት ማስፈን እንደሚስፈልግ ገልፀው አዲስ አበባ ሰፊ ቁጥር ያለው ወጣቶችና ሴቶችን በኢንተርፕራይዝ ተደራጅተው ስራ ፈጥረው ራሳቸውንና ወገኖቻቸውን እንዲጠቅሙ መቻሉን ገልፀዋል፡፡
የዛሬውን ጨምሮ ባለፉት አመታት ወደ ኢንደስትሪ የተሸጋገሩ 1625 ኢንተርፕራይዞች መሆናቸውን ገልፀው ከመንግስት የመጠበቅ ዝንባሌ መላቀቅ እንደሚያስፈልግ አስምረውበታል፡፡ ቢዝነሳቸውን ማስፋት ወደ አለም ገበያ መግባትና ተኪ ምርት ማምረት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡
በመጨረሻም ኢንደስትሪ ሽግግር እውን እንዲሆን ድጋፍ ላደረጉ አካላት አውቅና ተሰጥቷል፡፡