የአምራችነት ቀንን ምክንያት በፒያሳ አደባባይ ላይ የከተማ ግብርና ኤግዚቢሽን በይፋ ተከፍቷል፡፡
በምክትል ከንቲባና የሥራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ አላፊ አቶ ዣንጥራር አባይ ፣የአዲስ አበባ ከተማ ግብርና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ባዩ ሹጉጤን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በአገር ወስጥ አምራቾች የተዘጋጁ ምርቶች በቅናሽ ዋጋ የሚቀርቡበት ኤግዚቢሽን ተዘዋውረው በመመልከት አምራቾችን አበረታተዋል ።
ኤግዝብሽንና ባዛሩን ተዘዋውረው በጎበኙበት ወቅት ምክትል ከንቲባው ከተማ ግብርና ከተጀመረ አጭር ግዜ ቢሆንም የሕዝባችንን የፍጆታ ምርቶች ፍላጎትና ኑሮ ከማቃለል አንጻር እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ በእጅጉ ከፍተኛ በመሆኑ ለከተማ ግብርናን አስፈላጊውን ግብአት በማቅረብና በመደገፍ ምርታማነቱን በማሳደግ የከተማችንን ነዋሪዎች ሕይወት በዘላቂነት ማቃለል ይጠበቅብናል ብለዋል
የአገልግሎት፣የኢንተርፕራይዝና የኢንዱስትሪ ዘርፎችን በሁሉም ረገድ በመደገፍ ምርትና ምርታማነትን በሚፈለገው ደረጃ በማሳደግ የሀገራችንን ሁለንተናዊ ዕድገት በሚፈለገው ደረጃ በፍጥነት እውን እንዲሆን ለማድረግ በየደረጃው ያልተቋረጠ ቅንጅታዊ እንቅስቃሴ ማድረግና የየድርሻችንን ኃላፊነት መወጣት ይጠበቅብናል ብለዋል ምክትል ከንቲባው ።
የከተማ ግብርናን በሚፈለገው ደረጃ በማሳደግና መሸጫ ሥፍራዎችን በከተማችን ልዩ ልዩ አካባቢዎች በማበራከት ሰፊውን የአዲስ አበባ ነዋሪ እዚሁ በሚመረት የከተማ ግብርና ብቻ ተደራሽ ማድረግ መቻልን ጨምሮ በተጓዳኝ የአርሶአደሮቻችንን ሕይወት መቀየር እንችላለን ሲለ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል ።
የከተማ ግብርናን መደገፍ በከተማችን የኑሮ ወድነትን ለማቃለል ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚኖረው ሲሆን በሚፈለገው ደረጃ የገበያ ትስስርን መፈጠር ደግሞ አርሶ አደሮቻችንንም ታሳቢ ያደረገ ዕድገት ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው ሲሉ ምክትል ከንቲባው አስታውቀዋል።
በሁሉም ረገድ ምርትና ምርታማነታችንንና አጠቃላይ ልማታችንን ባልተቋረጠ መልኩ ለማስቀጠል የሀገር መከላከያ ሰራዊትና የጥምር ጦር አባላት የኢትዮጵያ ቀጣይነት አጽንተው ለማስቀጠል የሕይወት መስዋዕት እየከፈሉ የሚገኙበት ወቅት በመሆኑ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ በማድረግ አስተማማኝ የኋላ ደጀን መሆናችንን በተግባር ማረጋገጥ ይጠበቅብናል ብለዋል ።