ታሪካዊ የሆነው የማዘጋጃ ቤት ህንፃ እድሳት የአገልግሎት እድሜውን ከማርዘም ባሻገር ዘርፈ -ብዙ የሆኑ የአገልግሎት መስጫ መሰረተ -ልማቶች ተካተውለትና ስር ነቀል የሆነ እድሳት ተደርጎለት ለአገልግሎትና የከተማው ነዋሪዎች እንዲጎበኙት ከፍት ተደርጎ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ይህን ተከትሎ በተቋሙ ከሚሰሩ ሰራተኞችና ባለጉዳዮች መካከል የተወሰኑትን ስለ እድሳቱና ስለፈጠረባቸው ስሜት የሚከተለውን አጋርተውናል፡፡
ወ/ሮ ቅድስት መኮንን በህንፃው አስተዳደር ጽ/ቤት የፋሲሊቲ ቡድን መሪ ሲሆኑ በተቋሙ ብዙ አመታትን የሰሩ ናቸው፡፡ እሳቸው ለዝግጅት ክፍላችን እንደነገሩን፣ ህንፃው ቀደም ሲል የነበረው ውስጣዊ ድባብ ምቾት የሌለው ጨለማማ ከፍሎች ያሉት፣ በአንድ ጠባብ ክፍል ውስጥ በርካታ የሥራ ከፍሎች የነበሩበት፣ንፁህ ያልነበረና ንፅህናውን ለመጠበቅም ምቹ ሁኔታ የሌለው መሆኑን ጠቅሰው፤ እድሳት ከተደረገለት በኋላ በህንፃው ውስጥ ያለው ድባብ ንፁህና ደስ የሚል፣ ለሥራ ምቹና የተቋሙን እና የሰራተኛውን የሥራ ከባቢ የቀየረ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም “በውስጡ የተሰሩት የመፀዳጃ ቤት፣የመሬት ወለልና ሌሎች የእድሳት ሥራዎች ቆሻሻን የማይችሉ በመሆናቸው፤ ለንጽህና ሥራው ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው በማስቻላቸው፤ ለሰራተኛው ጤናም በጎ አስተዋፅኦ አድርገዋል”፡፡ በማለት ስለ እድሳቱ ያላቸውን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
ሌላይኛዋ አስተያየት ሰጪ የሆኑት የምስራች አለማየሁ በበኩላቸው፣ “ የተደረገው የእድሳት ሥራ የሚያምር አካባቢን የፈጠረ ከመሆኑ በሻገር፤ ቀልጣፋ ሥራን ለመስራት ይመቻል፡፡ በተጨማሪም ባለጉዳይና ሰራተኛን ግልፅ በሆነ ሁኔታ በቀላሉ ማገናኘት የሚያስችል ሆኖ መሰራቱ የአገልግሎት አሰጣጥን የሚያሻሽል አድርጎታል” በማለት ያላቸውን ሀሳብ አካፍለዋል፡፡
1. የእድሳት ሥራዎችን በሦስት ከፍሎ ማየት የሚቻል ሲሆን እነሱም መጠነኛ፣ መካከለኛ እና ስር ነቀል ወይም መልሶ መገንባት በሚባል ደረጃ (Renovation) በሆነ መልኩ የሚደረጉ የእድሳት ዓይነቶች እንዳሉ እና የከተማው ማዘጋጃ ቤት ከእነዚህ ሦስቱ የእድሳት ዓይነቶች ውስጥ ስር ነቀል እድሳት ተደርጎለታል።
ይህም ሲባል የህንፃው መዋቅር ሳይነካ መሰረታዊ በሆነ እና መልሶ መገንባት በሚባል ደረጃ የእድሳትና የማስዋብ ሥራ የተደረገለት ሲሆን የመገንቢያ ቁሳቁስ ዋጋና ጥራት እንዲሁም አሁናው የውጭ ምንዛሪን ተሳቢ ያደረገ ወጪ መሆኑ፤
2. ህንፃው ታሪካዊ ቅርስ እንደመሆኑ ይዘቱን ሳይለቅ በጥንቃቄ እንዲሰራ ፤ በውስጡ የተገጠሙለት ቁሳቁሶች ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ እና ዋጋቸው ያንን ተሳቢ ያደረገ መሆኑን፣
3. ለአካል ጉዳተኞች፣ለአቅመ ደካሞችና ሌሎች ድጋፍ ለሚሹ አካላት የሚስፈልጉ 8 (ስምንት) ዘመናዊ ድጋፍ ሰጪ ማሽኖች የተገጠሙለት መሆኑ፣
4. የህንፃው ውስጣዊ አሰራር ቀደም ሲል የነበረውን የአየር ንብረት፣ የሰው ብዛትና ሌሎች መሰል ሁኔታዎችን ተሳቢ አድርጎ የተሰራ በመሆኑ፤ አሁን ካለው ሁኔታ ጋር እንዲጣጣም በህንፃው ውስጥ ዘመናዊ የአየር ማስተካከያ (Air condition) የተገጠመለት መሆኑ፤
5. በህንፃው ውስጥ የነበሩት መፀዳጃ ቤቶች ሙሉ በሙሉ በአዲስ የተሰሩና በውስጡ ሊኖር የሚችል ሽታ ወደ ሥራ ክፍሎች እንዳይገባ መቅረፍ በሚያስችል ደረጃ መሰራቱ፤
6. የህንፃው ውስጥ አሌክትሪክ መስመሮች ሙሉ በሙሉ ከፍተኛ ጥራት ባላቸው መስመሮች መዘርጋቱና ቀደም ሲል የነበረውን ጨለማማ ድባብ የቀየሩ ዘመናዊ መብራቶች መገጠማቸው፣
7. የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከያ መሳሪያዎች በአዲስ መልክ መዘርጋቱ፣
8. አማራጭ የሀይል ምንጭ ሆኖ የሚሰራ ዘመናዊ ማሽን የተገጠመለት መሆኑ፣
9. ለተገልጋይና ለተቋሙ ሰራተኞች የሚያገለግሉ ምግብ ቤቶችና ካፍቴሪያዎች ሙሉ በሙሉ ከፍተኛ ጥራት ያላቸው የማብሰያና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸው ማሽኖች የተገጠሙለት መሆኑ፣
10. የከተማ አስተዳደሩ ከተማዋን የሚመጥን ተቋም እንደመሆኑ፤ ለአገልግሎት የሚውሉ ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ወንበሮች፣ ጠረጴዛዎች፣ ኮፒውተሮችና ሌሎች ቁሳቁሶች ሙሉ በሙሉ በዘመናዊና በአዲስ እንዲተኩ መደረጉ፣
11. ደረጃውን የጠበቀ የህፃናት ማቆያ ስፍራ፣ ቤተ- መጻሕፍትና ሌሎች በርካታ ግንባታዎች በአዲስ መልክ የተሰራለት ህንፃ ነው፡፡
ይህ ስር ነቀል የእድሳትና የማስዋብ ሥራ ወጪ የህንፃውን ስፋትና የምድረ ግቢ ሥራ ያካተተ ይኸውም የታተመ አርማታን (stamped concrete) ተግባራዊ በማድረግ፤ ቴክኖሎጂውን ጭምር በከተማ ደረጃ ለሚገነቡና ለሚሰሩ መንግስታዊና የግል ተቋማት ጭምር ለማስተዋወቅ ዘመኑን በዋጀና ዘመን ተሻጋሪ በሆነ ሁናቴ ተገንብቷል።
ከዚህም ጎን ለጎን አሁናዊ የውጭ ምንዛሪን ታሳቢ ያደረገ፣ ተጨማሪ እሴት ታክስን ያካተተ ወጪ የተደረገበት ግዙፍ ግንባታ ሲሆን የአገራችንና የአፍሪካ መዲና የሆነችው ከተማችን አዲስ አበባን በሚመጥን ልክ የተገነባ መሆኑን በአካል ተገኝቶ በማየት ምስክርነትን ሊሰጡበት የሚቻል ነው፡፡