በአዲስ ከተማ ክ/ከተማ  ያስጀመሯቸው የተለያዩ ፕሮጀክቶች በተለይም ዝቅተኛውን የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
ም/ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ ካስጀመሯቸው ፕሮጀክቶች ውስጥ በቀን 300,000 ሺህ ዳቦ ማምረት የሚችል የዳቦ ፋብሪካ አንዱ ሲሆን ይህ ፕሮጀክት በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ለህብረተሰቡ ዳቦ ማቅረብ እንደሚጀምርም ተነግሯል፤ በተጨማሪም በተጨናነቀና አስቸጋሪ ሁኔታ የሚኖሩ በመርካቶ ሰባተኛ አካባቢ የሚገኙ 16 መኖሪያ ቤቶችን እድሳትም ያስጀመሩ ሲሆን ሰራተኞች የመንግስት የስራ ሰዓትን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ለማስቻል የጣት አሻራ ፊርማ ቴክኖሎጂንም አስጀምረዋል፡፡
በዚህ ወቅት መልእክት ያስተላለፉት ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ ግማሾቻችን የተሻለ ህይወት እየኖርን ሌሎች ደግሞ በስቃይ እንዲኖሩ ኢትዮጵያዊነታችን ስለማይፈቅድ መደጋገፍ የዜጎችን ህይወት ለመለወጥ መስራትና አገልግሎት አሰጣጡን ማሻሸል ይኖርብናል ብለዋል፡፡