ትርፍን ሳያሰሉ የተለያዩ ህብረቀለማት የያዙ ክሮችን አሰናኝተው በሚለፉ የጥበበኛ እጆች የሚመረቱት ጥበቦች የድምቀታችንና የማንነታችን ሚስጥር ናቸው፤ ሀገራችንም የህብረብሔሮቿን ሀሳብ ቋንቋ ባህልና እምነት በአንድ አሰናኝታ የምትፈካ የብዙሀን የአብሮነት ውበት ማሳያ ናት!” ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ከ1ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርገውን የሽሮ ሜዳ የባህል አልባሳት መሸጫ የገበያ ማዕከልን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አደረጉ።በምርቃት መርሐግብሩ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እንደገለጹት የገበያ ማዕከሉ በእንጦጦ ፓርክ አቅራቢያ በመሆኑ ለጉብኝት የሚመጡ ቱሪስቶች የባህል አልባሳቱን በማቅረብ በዘርፉ ለተሰማሩ ዜጎች የገቢ ምንጭ እንደሚያሳድግ ጠቁመዋል ።

በገበያ ማዕከል ተጠቃሚ ወጣቶች ሕብረብሄራዊ፣ ደማቅ እና ውብ የሆነውን የኢትዮጵያዊ አልባሳትን የሚያጎላ በጥራት በማምረት ወደ ገበያው እንዲገቡ ወ/ሮ አዳነች ጥሪ አቅርበዋል ።

የሽሮሜዳ የባህል አልባሳት መሸጫ የገበያ ማዕከል 20,176 ካሬ ሜትር በሆነ ስፍራ ላይ የተገነባ ሲሆን ከ1ሺህ በላይ ለሚሆኑ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ከአስሩም ወረዳዎች የተውጣጡ ወጣቶች እና ሴቶች በማህበራት በማደራጀት እና 135 ለሚሆኑ ከዚህ በፊት ከሽሮሜዳ እንጦጦ በሚሰራው የመኪና መንገድ ማስፋፊያ ምክንያት የመስሪያ ቦታቸውን ላጡ ዜጎች ዳግም የስራ እድል ፈጥሯል።በጉለሌ ክፍለ ከተማ ሽሮ ሜዳ አካባቢ የተገነባው የባህል አልባሳት መሸጫ የገበያ ማዕከል 28 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ሲሆን 380 ሱቆችን የያዘ ነው ።