“የሀገር ተረካቢነታችንን በአረንጓዴ አሻራችን ኢትዮጵያንችንን እናልብስ” በሚል ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ከ30ሺህ በላይ ተማሪዎች ፣መምህራን እና የትምህርት ማህበረሰብ አመራሮች ችግኞችን ተተክለዋል ።
ተማሪ እያለን ሰኔ 30 ዓመቱን ሙሉ የተማርነውን ውጤት ለማወቅ በጉጉት የምንጠብቀው ቀን ነው ያሉት ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ዛሬ ደግሞ ተማሪዎች ኢትዮጵያን እናልብሳት በማለት ችግኝ በመትከል አሻራ ማኖራቸውን ገልጸዋል::
ዛሬ የተተከሉ ችግኞችም ለነገይቱ ኢትዮጵያ እና ለአዲስ አበባ ልምላሜ የተላበሰች ፣ ለኑሮ የተመቸች እንድትሆን የሚያደርግ በመሆኑ ተማሪዎች ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን መኮትኮት እና መንከባከብ ይገባል ሲሉ ምክትል ከንቲባዋ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ።
በዛሬው ዕለት በከተማዋ በሁሉም የመንግሥት እና የግል ትምህርት ቤቶች በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐግብር ከ100ሺህ በላይ ችግኞች እንደሚተኩ የአዲስ አበባ ከተማ ትምሀርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ ገልጸዋል ።