“የሕይወት ልምዴን አካፍላለሁ ” በሚል መሪ ቃል ውጤታማ ሴቶች የህይወት ልምዳቸውን የሚያካፍሉበትና ሴቶች በሀገር ግንባታ ስለሚኖራቸው ተሳትፎ እና ሚና በተመለከተ ውይይት ተካሂዷል ።
በዉይይት መድረኩ ተገኝተው የህይወት ልምዳቸውን ያካፈሉት ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ሴቶች ችግሮችን ተጋፍጦ መፍታት እንጂ መሸሽ ውጤት አያመጣም ያሉ ሲሆን ለዚህም ሴቶች ችግሮችን የመፍታት እና የመጋፈጥ ልምዳችንን ማዳበር ይኖርብናል ብለዋል ።
ችግሮችን ተጋፍጦ ወደ እድል መቀየር በዓለማችን ላይ የሚገኙ ብርቅዬ ሴቶች መለያ በመሆኑ በራስ መተማመንን ማዳበር፣ ችሎታን መለየትና እችላለሁ ብሎ መሞከር ሴቶችን ለተሻለ ስኬት ሊያበቃቸው ይችላል ብለዋል።
ወደ ለዉጥና ስኬት ለመድረስ ሴቶች ውስብስብ ፈተናዎችን ተጋፍጠው ማለፍ እንደሚጠበቅባቸው የገለፁት ምክትል ከንቲባዋ የሚያጋጥማቸውን ተግዳሮቶች በጽናት ማለፍ ይጠበቅባችኋል ብለዋል ።
ችግሮች ሲያጋጥሙ ሌሎችን ከመውቀስ ይልቅ መፍትሔው ላይ ጊዜያችሁን ማጥፋት ይኖርባችኋል ያሉት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ከሌሎች ጠንካራ ሰዎች የሕይወት ልምዶችን በመቅሰም ለጉዟችሁ እንደ ስንቅ መጠቀም አለባችሁ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።