የገቢዎች ሚኒስትር ፣የጉሙሩክ ኮሚሽን እና የብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር በጋራ ሆነው ባዋጡት የ10 ሚሊየን ብር በመመደብ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ለሚገኙ የ101 አቅመ ደካሞች የቤት እድሳት ስራን በየካ ክፍለ ከተማ አስጀምረዋል ።
የቤቶቹን እድሳት በይፋ ያስጀመሩት ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እንዳስታወቁት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራ ከለውጡ ማግስት ባህል ሆኖ እየዳበረ ቀጥሏል ብለዋል፡፡
የፌደራል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እና የተለያዩ ተቋማት በክረምት በጎፍቃድ አገልግሎት ተሳታፊ በመሆን ማህበራዊ ኃላፊነታቸው በመወጣት ለህዝቡ አለኝታነታቸውን በማሳየት ላይ እንደሚገኙ ምክትል ከንቲባዋ ገልጸዋል፡፡
በዘንድሮው የክረምት ወራት በጎፍቃድ አገልግሎት በከተማዋ ከ2ሺህ በላይ የአቅመ ደካማ ዜጎችን ቤት ለማደስ በተያዘው እቅድ መሰረት በስካሁም ከ750 በላይ ቤቶች እድሳት መጀመሩን እና ከ250 በላይ ቤቶች መጠናቀቁን ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ጠቁመዋል፡፡
ይህ በጎ ተግባር ለመፈጸም መልካም ልብ ያስፈልጋል ያሉት የመተሳሳብ እና የመረዳዳት መንፈስን በማዳበር ነው ያሉት ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የገቢዎች ሚኒስቴር ፣ጉሙሩክ ኮሚሽን እና ተጠሪ ተቋማት የልማት ስራዎች እንዲፋጠኑ እና በራሳችን ወጪ እንዲሸፈኑ ገቢ ከመፍጠር ባለፈ በማህበራዊ አገልግሎት በተለያዩ በጎ ተግባራት በመሳተፍ እያደረገ ያለው ከፍተኛ ጥረት ሊበረታታ እና ሊመሰገን ይገባል ብለዋል፡፡
የገቢዎች ሚኒስትሩ አቶ ላቅ አያሌው በበኩላቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የነዋሪውን ኑሮ ለማሻሻል እያደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ መስሪያ ቤታቸው ሰራተኞችን በማስተባበር ሕብረተሰብ ተኮር በሆኑ ስራዎች ላይ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን እንገኛለን ብለዋል፡፡
በዛሬው ዕለትም ለ101 የአቅመ ደካማ ነዋሪ የሆኑ ቤቶችን እድሳት በይፋ ጀምረናል ፤ቤቶችን በፍጥነት አጠናቀን ለነዋሪዎች ለማስረከብ እንሰራልን ብለዋል አቶ ላቅ አያሌው፡፡