የዘንድሮውን የክረምት ወራት በጎፍቃድ አገልግሎት 100 ህጻናትን በጉዲፈቻ ፣ባሉበት ሆነው ለማድረግ እና በሌሎች አማራጮች ድጋፍ ለማድረግ እቅድ መያዙን የገለጹት ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ከፍተኛ አመራሮች ፣የሴክተር ተቋማት እና ባለሀብቶች በጠቅላላው 306 ህጻናት በጉዲፈቻነት ወላጅ እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል።
ዛሬ በጉዲፈቻነት የወሰድናቸውን ልጆች ልክ እንደ ቤተሰብ በአካል ፣በአዕምሮና ስነልቦና የተሟላ እድገት እንዲኖራቸው ሃላፊነታችንን እንወጣለን ያሉት ምክትል ከንቲባዋ እንዚህን ልጆች ለማሳደግ የተረከባችሁ አመራሮች እና ባለሀብቶች ያደረጋችሁት ተግባር ምሳሌነት ያለው በመሆኑ ልትመሰገኑ ይገባል ብለዋል።
ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በጉዲፈቻ ለተረከቧት ሕፃን ዲቦራ የሚል መጠሪያ ስም ያወጡላት ሲሆን ከልጆቻቸው ጋር እኩል ሊያሳድጓትም ቃል ገብተዋል።
ነገ ልናጭድ የምንችለው ዛሬ የሰዘራነውን ትውልድ ነው ያሉት ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ይሄ ተግባራችን ዛሬያችንን ብቻ ሳይሆን ነገያችንን ጭምር የሚያሳምር በመሆኑ ትውልድ ግንባታ ላይ ሁሉም ሊረባረብ እንደሚገባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ጠቁመዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና በጎ ፍቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብራሃም ታደሰ በርክክብ መርሐግብር እንደገለጹት እነዚህን ህጻናትን ለመንከባከብ ባለሀብቶች ፣የሴክተር ተቋማት እና የተቋማት አመራሮች በጠቅላላው ከ13ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች እና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሃዳስ ኪዱ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ቢሮው ወላጅ አልባ ህጻናትን በሀገር ውስጥ እና የውጪ ሀገር ጉዲፈቻን እንዲያገኙ የዛሬውን ጨምሮ በአጠቃላይ 1 ሺ 350 ህጻናት በጉዲፈቻ አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን ገልጸዋል ።
በዛሬው ዕለትም ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች፣ የካቢኔ አባላት እና የተለያዩ የሴክተር መስሪያ ቤቶች እንዲሁም ክፍለ ከተሞች ህጻናትን በጉዲፈቻ ለማሳደግ እና በስፖንሰር ለመንከባከብ ርክክብ አድርገዋል፡፡