ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በዛሬው እለት ከኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለፁት በአዲስ አበባ ከሽብር ሃይሎቹ የኦነግ ሸኔ ፤የፅንፈኛ ሃይሎች ከወያኔ ስምሪትና መልእክት የሚቀበሉና የሚያቀብሉ ከ1500 በላይ ለጥፋት የተሰማሩ ሃይሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቀዋል፡፡
እነዚህ ሶስት አካላት ተናበው ይሰራሉ ተብለው የማይገመቱ ጭምር በመናበብ በከተማዋ የጥፋት ተግባር ለመፈፀም የተለያየ መታወቂያዎችን በመጠቀም ሲንቀሳቀሱ መያዛቸውን ከንቲባዋ የገለፁ ሲሆን በርካታ መሳርያዎችም ጭምር ከበቂ ማስረጃ ጋር በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና በቅርብ የፀጥታ ግብረ ሃይሉ የአዲስ አበባ ፖሊስ መግለጫ እንደሚሰጥበት ገልፀዋል፡፡
ህዝባችን ይጠቁማል ያጋልጣል ያሉት ከንቲባ አዳነች ህዝባችን ምስጋና ይገባዋል ብለዋል፡፡ ህዝቡ ራሱን አጋልጦ ያጋልጣል ፤ ከተማውን ይጠብቃልም ብለዋል፡፡ የፀጥታ ሃይሉም የሚገባውን ሁሉ ዋጋ እየከፈለ የከተማዋን ሰላም ለማስጠበቅ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ህዝቡ ከዚህ በፊት ወንጀለኞችን ትይዛላችሁ ነገር ግን ለፍርድ አታቀርቡም የሚል ወቀሳ ይሰነዘር እንደበር አውስተው ፤አሁን እነኚህን አካላት በተደራጀ መንገድ ወደ ፍርድ ቤት እየቀረቡ መሆኑንና የፍትህ አካላትም በተደራጀ መንገድ እየሰሩበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡