በአከባበሩ ስነስርዓት ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈጉባኤ ወ/ሮ ቡዜና አልቃድር እንዲሁም አቶ ጃንጥራር አባይ የአዲስ አበባ ከተማ ም/ከንቲባና የስራ ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ሀላፊ እንዲሁም ሌሎች የምክር ቤቱና የከተማ አስተዳደሩ አመራሮችና ሰራተኞች ተገኝተዋል።
አቶ ጃንጥራር አባይ በዚሁ ስነስርዓት ላይ ከተናገሩት :-

“ዜጎች ለሀገራቸው ያላቸው ፍቅርና ብሔራዊ ስሜት ለሰንደቅ ዓላማ በሚሰጡት ክብር ይገለጻል፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ለሰንድቅ ዓላማ የምንሰጠው ፍቅርና ክብር ከናት ካባቶቻችን በክብር የወረስነው ለቀጣዩ ትውልድ በክብር የምናወርሰው በልባችን ውስጥ ታትሞ የሚቆይ የብዝሀነታችንና የአንድነታችን የሉዓላዊነታችን መገለጫ ታላቅ ሀገራዊ ዕሴት ነው፡፡

ሰንደቅ ዓላማችን የግዛት አንድነት ፣ የአብሮነት የብሔራዊ መግባባት መገለጫ ዓርማችን በመሆኑ ማንኛውም ዜጋ ለሰንደቅ ዓላማ ክብር መስጠት የማክበርና የማስከበር ኃላፊነት አለበት ፡፡

የውስጥ ቅጥረኞችና ተላላኪዎቻቸው ብሔራዊ አንድነታችንን ሉዓላዊነታችንን አደጋ ላይ ለመጣል እየሰሩ ባለበት በዚህ ወቅት ሰንደቅ ዓላማ ቀን መከበሩ ለሕበረ ብሄራዊ አንድነታችን መጠናከርና መነቃቃት ትልቅ ትርጉም አለው

በዓሉን ስናከብር ለሀገር ሉዓላዊነትና ጥቅም መከበር ዳግም ቃልኪዳንናችንን የምናድስበት ነው
ባንዲራችንየህዝባችን የደም ውጤት ነው፡፡

ዛሬም ለባንዲራችን ድሙን እያፈሰሰ ያለው የሀገራችን መከታ ጀግናው መከላከያ ሠራዊታችን በዓላችንን በድምቀት እንድናከከብር አድርገውናልና እናመሰግናቸዋለን!

በኢትዮጵያዊ አንድነታችን ጸንተን የተጋረጠብንን አደጋ በጋራ በመመከት የሀገራችንን ሕልውና ላለማስደፈር በየትኛውም ጊዜ መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ሆነን ባንዲራችንን ከፍ አድርገን የምንሰቅል በአንድንት ቆመን ለጠላት የማንበገር ኢትዮጵያውያን ነን፡፡