ይህንኑ ጉዳይ አስመልክቶ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የስራ፣ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ ወቅት እንደገለፁት፤ የኢንዱስትሪ ክላስተር ወይም ስማርት ኢንዱስትሪያል ከተማ የሚል ፕሮጀክት በአቃቂ ክፍለ ከተማ በ93 ሄክታር መሬት ላይ የኢንዱስትሪ ክላስተር ለመገንባት የታቀደ ሲሆን በዘንድሮ አመት በ42 ነጥብ 6 ሄክታር የሚገነባ ልማት ለመጀመር ቅድመ ሁኔታዎችን በመጠናቀቅ ላይ ናቸው ብለዋል ፡፡
አክለውም ከተማ አስተዳደሩ እያስገነባቸው ከሚገኙ ሜጋ ፕሮጀክቶች መካከል የሆነው ይህ ስራ ጨረታው አልቆ ወደ ተግባር እየተገባ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
መዲናዋ እስከ አሁን ድረስ የራሷ የሆነ ኢንዱስትሪ መንደር እንዳልነበራትና ያሉትም በፌዴራል የሚተዳደሩ መሆናቸውን ያስታወሱት ምክትል ከንቲባው፣ በክላስተር የለሙና ሼድ የተገነባላቸው የራሳችን ኢንዱስትሪ ፓርክ የምንለው እንደ ከተማ አልነበረንም ሲሉም ገልፀዋል።
አያይዘውም ወደ ትግበራ እየተገባበት የሚገኘውና ለከተማዋ ጉልህ ጠቀሜታ የሚኖረው ይህ ፕሮጀክት፣ የኢንተርፕራይዞች የሽግግር ማሳለጫነቱ እጅጉን የታመነበት የከተማው አስተዳደር ግዙፍ የልማት እቅዶች አካል መሆኑን ጨምረው አብራርተዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ በትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ጽ/ቤቱ አማካይነት ካስገነባቸውና በግንባታ ሂደት ላይ ከሚገኙት ሜጋ ፕሮጀክቶች በተጨማሪ በ2015 በጀት አመትም በተቋሙ በኩል በርካታ ሰው ተኮር ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን እውን ለማድረግ በዝግጅት ላይ ይገኛል።