የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ፍላጎት ያላቸውን ነባር የ20/80 እና የ40/60 የማህበር ቤት ፈላጊዎችን በህብረት ስራ ማህበር ተደራጅተው እንዲሰሩ በኦንላይን ምዝገባ ማካሄዱ የሚታወቅ ነው፡፡
ቢሮውም ካሉት አማራጭ የቤት አቅርቦት ውስጥ አንዱ የሆነውን የማህበር ቤት ተግባራዊ ለማድረግ የዲዛይን ዝግጅት ፣ የመሬት ዝግጅት እና የአበዳሪ ባንኮችን የመለየት ቅድመ ሁኔታዎችን በማጠናቀቅ ማህበራቱ ተደራጅተው ወደ ተግባር የሚገቡበትን ሁኔታ ማመቻቸቱን አሳውቋል፡፡
የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮም በኦንላይን የተመዘገባችሁ የ20/80 እና የ40 /60 ቤት ፈላጊዎች አስፈላጊውን መረጃ እንድታሟሉ ሲል ጠይቋል፡፡
በመሆኑም ከዚህ በፊት በኦንላይን የተመዘገባችሁ የማህበር ቤቱ ፈላጊዎች ሁሉ “በአዲስ አበባ ከተማ በራሳችሁም ሆነ በትዳር አጋራችሁ ስም ቤት ወይም ቤት መስሪያ ቦታ የሌላችሁ ወይም ኖሯችሁ ከ1997 ዓ.ም ወዲህ በስጦታ ወይም በሽያጭ ያላስተላለፋችሁ መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ” የሚገልፅ ቅፅ ከምትኖሩበት ወረዳ ቤቶች አስተዳደር ጽ/ቤት በመውሰድ ከየካቲት 16 እስከ መጋቢት 16 / 2014 ዓ.ም ድረስ በኦንላይን የተደረገውን ምዝገባ በአካል እንድታረጋግጡ ብሏል፡፡
ቢሮው ሁሉም ተመዝጋቢ ከላይ በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ ውስጥ ማስረጃውን ማቅረብ እንደሚጠበቅበትና ጊዜውን አሳልፈው ለሚመጡ ኃላፊነት እንደማይወስድ አሳስቧል።