በተለያዩ ክፍለ ከተሞች በጦር መሳሪያ ዝውውር በተጠረጠሩ ግለሰቦች መኖሪያ ቤት በተደረገ ብርበራ 9 ሽጉጦች እና በተሽከርካሪ ውስጥ ተደብቆ ሲጓጓዝ የነበረ 16 ቦንብ ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመተባበር ከነተጠርጣሪዎቹ ተይዘው ምርመራ እየተጣራ ይገኛል፡፡
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 እና 14 ከህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ጋር በተያያዘ 4 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራ ይገኛል፡፡ የአዲስ አበባ ፖሊስ እንዳስታወቀው ህብረተሰቡ በሰጠው ጥቆማ እና በፖሊስ ክትትል በተጠቀሱት ወረዳዎች ነዋሪ በሆኑ እና በወንጀሉ በተጠረጠሩ 2 ግለሰቦች መኖሪያ ቤት በተደረገ ብርበራ 5 የተለያዩ ሽጉጦች እና 53 ልዩ ልዩ የሽጉጥ ጥይቶች ተይዘዋል፡፡
በተመሳሳይ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ሚኪሊላንድ ኮንደሚኒየም ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኝ የጋራ መኖሪያ ቤት ውስጥ የአዲስ አበባ ፖሊስ እና የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ባደረጉት ክትትል 4 ሽጉጥ ከ30 መሰል ጥይት እና 1 የእጅ ቦንብ በብርበራ ተይዟል፡፡ በዚህ ወንጀል የተጠረጠሩ 4 ግለሰቦችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጿል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 በተለምዶ ፊናንስ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የአዲስ አበባ ፖሊስ እና የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ባደረጉት ክትትል የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 5-01928 አ.አ በሆነ ፒካፕ ተሽከርካሪ አካል ውስጥ ተደብቆ ሲጓጓዝ የነበረ 15 የእጅ ቦንብ ከ3 ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር ውሏል።
በአጠቃላይ 16 የእጅ ቦንብ፣ 9 ሽጉጥ እና 83 የተለያዩ የሽጉጥ ጥይቶችን ከ11 ተጠርጣሪዎች ጋር ይዞ ምርመራ እያጣራ እንደሚገኝ የገለፀው የአዲስ አበባ ፖሊስ በህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ላይ የሚያደርገውን ክትትል እና ቁጥጥር አጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ፖሊስ እያስታወቀ ህብረተሰቡ አሁንም አካባቢውን ከፀረ ሰላም ሃይሎች በንቃት እንዲጠብቅ እና ጥቆማና መረጃ በመስጠት ለፀጥታ አካላት እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን አቅርቧል