በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የመሬትና መሬት ነክ አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ያሉ ችግሮችን ለማስተካከል የተለያዩ አስተዳደራዊ እርምጃዎች እየተወዱ መሆናቸው ይታወቃል። ይህን ተከትሎ ከክፍለ ከተማ እስከ ወረዳ ያሉ የመሬትና መሬት ነክ አገልግሎቶች ለጊዜው እንዲቆሙ ተደርገው የተለያዩ ማጣራቶች እየተደረጉ ይገኛሉ።
በክፍለ ከተማዉ ዋነኛዉና ወሳኝ የህዝብ ጥያቄ የሆነዉን የመሬት አገልግሎት ጥያቄዎች በህጋዊ መንገድ ለመመለስ የማስተካከያ እርምጃዎች እየተወሰዱ ባለበት በዚህ ወቅት በትናንትናው ዕለት 18/12/2014 ዓ.ም በለሚ ኩራ ክ/ከተማ ወረዳ 13 ልዩ ስሙ ምስራቅ ሎቄ (የወረዳ መሻገሪያ) በሚባል ቦታ የየካ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማት አስተዳደር ሠራተኛ የሆነች አንዲት ግለሠብ የክፍለ ከተማው ንብረት የሆነውን ጂ.ፒ.ኤስ ከአስተዳደሩ እውቅና ውጭ በመጠቀም የመንግስትና የህዝብ ንብረት የሆነውን መሬት ልኬት በመውሰድ ለግለሠብ ጥቅም ለማዋል ስትሞክር ከሦስት ባለ ጉዳዮች ጋር በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ግለሰቧ በመንግስት የተሰጣቸውን ኃላፊነት እና ሙያዊ ስነ-ምግባር ወደ ኋላ በመተው እና በመጣስ እንዲሁም የለሚ ኩራ ክፍለከተማ ነባራዊ ሁኔታን ሽፋን በማድረግ ለግለሠቦች ጥቅም ሲባል የመንግስት እና የህዝብ ሀብትን ለመቀራመት እንዲሁም ላልታለመለት አላማ እና ተግባር እንዲውል በማድረግ ሙከራ ነዉ በቁጥጥር ስር የዋሉት።
የክ/ከተማ አስተዳደሩም በህግ ጥላ ስር የዋሉት ግለሠቦችን የፍርድ ሂደት ተከታትሎ ውጤቱን ለህዝብ እንደሚያሳውቅ ገልጿል።