የመከላከያ መረጃ ዋና መምሪያ፣ የአዲስ አበባ ሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ በመቀናጀት ባካሄዱት ኦፕሬሽን ግለሰቦቹ ለህገ ወጥ ተግባሩ ሲጠቀሙባቸው የነበሩ ልዩ ልዩ ኤግዚቢቶች ተይዘዋል፡፡
ግለሰቦቹ ህገ ወጥ ድርጊቱን ሲፈጽሙ በነበረበት ቤት ህገ ወጥ ገንዘቡን ለማተም የሚጠቀሙበት ማሽን ፣ ኬሚካሎች ፣ መጠኑ በውል ያልታወቀ የውጭ ሀገር እና የኢትዮጵያ ገንዘብ፣ ታትመው ለመሰራጨት የተዘጋጁ ህገ ወጥ ገንዘቦች፣ ህገ ወጥ ገንዘቡን ለማተም የተዘጋጁ የተለያየ ቀለም ያላቸው ወረቀቶች ጨምሮ የተለያዩ ኤግዚቢቶች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
እንዲሁም በአቃቂ ቃሊቲ ፣ የካ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ ጉለሌ እና አራዳ ክፍለ ከተሞች ሀሰተኛ ሰነዶችን በመስራት ተግባር ላይ የተሰማሩ 10 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ሀሰተኛ ሰነዶችን በማዘጋጀት እና በማሰራጨት እንዲሁም የተለያዩ ወረዳዎችን እና ክፍለ ከተሞችን ተቋማት ማህተሞች እና የሀላፊዎችን ቲተሮች አስመስለው በመስራት ሀሰተኛ የመንግስት እና የግል የትምህርት ማስረጃዎችን፣ የመሬት የይዞታ ማረጋገጫ ካርታዎችን፣ ሀሰተኛ የከተማ አስተዳደሩን የነዋሪነት መታወቂያዎችን ፣ የልደት ሰርተፍኬት እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማረጋገጫ ማህተምና ቲተርን አዘጋጅተው ሲያሰራጩ በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
ሀሰተኛ የመሬት ካርታዎቹን በዋነኝነት ለህገ ወጥ መሬት ወራሪዎች እና የተለያዩ ግለሰቦችን ለማጭበርበር ሲጠቀሙባቸው እንደነበሩ እና ሀሰተኛ መታወቂያዎቹን ደግሞ በተለይ ከተለያዩ አካባቢዎች በህገ ወጥ ተግባር ላይ ተሰማርተው ወደ ከተማዋ ለመጡ ግለሰቦች ከ1500 ብር እስከ 3000 ብር ሲሸጡ ቆይተዋል፡፡