በዛሬው እለት የልደታ ክ/ከተማ በህዝብና በመንግስት የጋራ ጥረት ሲገነቡ የቆዩ ከ162 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው 82 ፕሮጀክቶች ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በተገኙበት ተመርቀዋል፡፡
በፕሮጀክቶቹ ምርቃት ስነስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እንደተናገሩት ለህዝብ ትንሽ የሚባል ፕሮጀክት የሉም ያሉ ሲሆን በተለይም የትውልድ መገንቢያ የሆኑ ትምህርት ቤቶች ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።
እነዚህ ፕሮጀክቶች በህዝብ ምክር ቤቶች አጀንዳ ሆነው ይቀርቡ እንደነበር ያስታወሱት ክብርት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች የተናገርነውን ቃላችንን መጠበቅ በመቻላችን ደስ ብሎናል ሲሉ ገልፀዋል፡፡
እንደ ከንቲባ አዳነች ፕሮጀክቶቹ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነን ያሳካነው ፕሮጀክት ነው ያሉ ሲሆን ይህም ምንም ውዥንብር ቢኖር ፤ምንም አይነት ተግዳሮትና ፈተና ቢኖር፤ ሊያስቆመን እንደማይችል ማሳያ ነው። ዋናው ነገር መስራት ፤ መደማመጥ መተማመን ነው የሚጠበቅብን ብለዋል፡፡
እነዚህ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያ በድል እየቀጠለች እንደሆነች ማሳያዎችም ናቸው ያሉት ከንቲባ አዳነች ህዝቡ ሰርተን እስካሳየነው ድረስ ይደግፈናል፤ ከጎናችንም ይቆማል ብለዋል፡፡
ጀመርን እንጂ ገና ብዙ እንሰራለን፤ 24 /7 ወደ ኋላ የሚመለስ አይደለም ለአንድና ለሁለት ፕሮጀክቶች ሳይሆን ፤መርሃችን መሆኑን አውቃችሁ፤አግዙን እንሰራ ብለዋል፡፡
የልደታ ክ/ከተማ ዋና ሰራ አስፈፃሚ አቶ አሰግደው ሃ/ጊዮርጊስ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት እነዚህን ፕሮጀክቶች ሙሉ ለመሉ አጠናቀን ለው ለምርቃት ያበቃናቸው ያሉ ሲሆን ይህ እውን እንዲሆን የአመራር ፤የባለሙያና የህዝብ ጥረት የጋራ ውጤት ነው በማለት ገልፀዋል፡፡