የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጥናቱ ከተለየ 1,338 ሄክታር መሬት ውስጥ 1,050 ሄክታር ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ የተደረገ መሆኑን ም/ል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ።የአዲስ አበባ ከተማ ም/ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በጋዜጣዊ መግለጫቸው እንዳመላከቱት በከተማዋ በህገ-ወጥ ወረራ የተያዘው መሬት 1,338 ሄክታር ሲሆን በገንዘብ ሲተመን በ14 ቢሊየን ብር የሚገመት መሆኑንና የህዝብና የመንግስት ሀብት በሪል ስቴት አልሚዎች፣ በግለሰቦች፣ በሀይማኖት ተቋማትና በቡድን በመደራጀትና መንደር በመመስረት ጭምር በሚገለፅ መልኩ የመሬት ወረራ ተፈፅሟል፡፡
በወረራ ከተያዘውና በጥናቱ ከተለዩ 1,338 ሄክታር መሬት ውስጥ 1,050 ሄክታር የሚሆን መሬት እንዲፀዳ በማድረግ ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ ተደርጓል።ወ/ሮ አዳነች አቤቤ አክለው የቀረው መሬት በቀጣይ የከተማውን ልማት በሚያረጋገጥ መልኩ በሊዝና ለትልልቅ የልማት ስራዎች በጨረታ ጥቅም ላይ እንዲውል ይደረጋል ብለዋል፡፡በህገወጥ መልኩ የተያዙ የጋራ መኖርያ ቤቶችን አስመልክቶ በማስለቀቅ ተጠቃሚ ለመሆን ተመዝግበው ለሚገኙ ዜጎች የማስተላለፍ ስራ እንዲሁም የቀበሌ የመኖሪያና የንግድ ቤቶችንም ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን በሚያሰፍን አግባብ እንዲፈፀም ይደረጋል ሲሉ ወ/ሮ አዳነች ገልፀዋል፡፡
ጥናቱን መነሻ በማድረግ በህገወጥ መልኩ የተያዙ ቤቶችን ህግንና ስርአትን የማስከበር ስራ በመስራት በከፋ የቤት ችግር ውስጥ ላሉ ወገኖች እንዲተላለፉ ይደረጋል ያሉት ወ/ሮ አዳነች ሌላ በኩል ከፍተኛ ሀብት ያካበቱ ግን ደግሞ በመንግስት የቀበሌ ንግድ ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ነጋዴዎችንም በማስለቀቅ ፍትሀዊ የንግድ ስርአቱን ለማስጠበቅ በሚያስችልና ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍልንም በሚያረጋግጥ መልኩ የሚፈፀም ይሆናል ብለዋል::
በከተማው በተካሄደ ጥናት ግኝት መነሻነት በህግ መጠየቅ ያለባቸው አካላት እንዲጠየቁ ለማድረግ ለፌዴራል አቃቤህግና ለፖሊስ ደብዳቤ መፃፋቸውን እና እስከመጨረሻው የሚከታተሉ መሆኑን ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ገለፀዋል።