በአዲስ አበባ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 በ50 ሚሊየን ብር ወጪ ለሚገነባው ትምህርት ቤት ብፁዕ ካርዲናል ብርሀነኢየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ካርዲናል ብርሀነኢየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን እንደተናገሩት÷ ትምህርት ቤት ከሐይማኖት ተቋማት ቀጥሎ የሰው ስብዕና ከሚቀረጽባቸው ማዕከላት መካከል አንዱ እና ዋነኛው ነው፡፡
በመሆኑ በስፍራው የትምህርት ቤት ግንባታ ስራ መጀመሩ መልካም ተግባር መሆኑን መግለፃቸውን ከክፍለ ከተማው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ፍሬህይወት ሽፈራው በበኩላቸው÷ በወረዳው የትምህርት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ መሰል የትምህርት ቤት ግንባታ እና ማስፋፊያዎች ጉልህ ድርሻ ስላላቸው ትምህርት ቤቱ ተጀምሮ እስከሚያልቅ ድረስ የወረዳ አስተዳደሩ ከጎናቸው እንደማይለይ አረጋግጠዋል፡፡
የትምህርት ቤቱ ግንባታ ስራ የሚከናወነው በኢንጌጅመንት ግሎባል ፈንድ እና የካፑቹን ማህበር ትብብር ሲሆን÷ 50 ሚሊየን በሚገመት ወጪ በሁለት አመት ውስጥ ግንባታው ተጠናቆ ለአገልግሎት ይበቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
(ኤፍ ቢ ሲ)