የመዲናዋ ነዋሪዎች ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችን በመጠቆም ረገድ አበረታች ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑንም ነው ኮሚሽኑ ያስታወቀው፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ ለኢዜአ እንዳሉት በመዲናዋ ጥቆማን መሰረት ተደርጎ በተከናወነ ፍተሻ በርካታ የሀሰተኛ ሰነዶች እና የጦር መሳሪያዎች ተይዘዋል ብለዋል።
በተለያዩ አካባቢዎችም የጦር መሳሪያዎችና ተተኳሽ ጥይቶች በቆሻሻ ገንዳ ውስጥ ተጥለው እየተገኙ እንደሆነም ገልጸዋል።
የህወሃትና ሸኔ አሸባሪ ቡድኖችን ዓላማ ለማስፈጸም ራሳቸውን ቀይረው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ግለሰቦች ከያዟቸው የሬድዮ መገናኛ እና የሳተላይት ስልኮች ጋር በህብረተሰቡ ጥቆማ በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ጠቁመዋል።
በዚህም የአሸባሪ ቡድኖቹ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምን ለማወክ ይዘውት የነበረው እቅድ ማክሸፍ መቻሉን አውስተዋል፡፡
በዚህ ሁሉ ሂደት የመዲናዋ ነዋሪዎች ያደረጉት ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
አሸባሪው ህወሃት ህዝብን ለማሸበር የሚጠቀምበት ዋነኛው ዘዴ ሀሰተኛ መረጃን ማሰራጨት መሆኑን ገልጸው፤ ከሰሞኑም በመዲናዋ ብሔርን መሰረት ያደረገ እስር እየተከናወነ በማስመሰል ሀሰተኛ መረጃ እያሰራጨ ይገኛል ነው ያለት፡፡
ፖሊስ ጥንቃቄ በተሞላበት አካሄድ የአሸባሪ ቡድኖችን ዓላማ ለማስፈጸም እንደሚንቀሳቀሱ የሚጠረጠሩ ግለሰቦችን ለይቶ በቁጥጥር ስር እንደሚያውል ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ ውንጀላው መሰረተ ቢስ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ህብረተሰቡ ህገ-ወጦችን በማጋለጥ በኩል እያደረገ ያለውን ተሳትፎ አድንቀው፤ ይህንን ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥልም ነው ኮማንደር ፋሲካ ጥሪ ያቀረቡት፡፡
በተለይ ወጣቶች አካባቢያቸውን ነቅተው በመጠበቅ ለመዲናዋ ሰላም መጠበቅ እያበረከቱት ያለውን ሚና አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡
ኢዜአ
-አካባቢህን ጠብቅ
_ ወደ ግንባር ዝመት
_ መከላከያን ደግፍ