በተሽከርካሪ አካል ውስጥ ተደብቆ ወደ አዲስ አበባ የገባ ከ6 ሺህ በላይ የክላሽ ጥይት እና የብሬን ዝናር ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመተባበር መያዙን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
መነሻውን ባህርዳር ከተማ ያደረገ የሰሌዳ ቁጥር 04240 ኮድ 3 አ.ማ ላንድ ሮቨር ተሽከርካሪ አካል ውስጥ ተደብቆ ወደ አዲስ አበባ የገባ ብዛቱ 6985 የክላሽ ጥይት እና እያንዳንዱ 492 የብሬን ጥይት መያዝ የሚችል አራት የብሬን ዝናር በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ልዩ ቦታው አዲሱ ገበያ ድል በር አካባቢ ታህሳስ 9 ቀን 2014 ዓ/ም ከቀኑ 11፡00 ሰዓት ላይ ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመተባበር እጅ ከፍንጅ እንደተያዘ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
ጥይቱን ሲያዘዋውሩ የተገኙ ሁለት ተጠርጣሪዎች እና ለህገ-ወጥ ተግባር የተገለገሉበት አንድ ተሽከርካሪ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራው እየተጠራ መሆኑን ፖሊስ ገልጿል፡፡
የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪዎች ልዩ ልዩ ስልቶችን በመጠቀም የህብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት ስጋት ውስጥ ለመጣል እየሰሩ መሆናቸውን ያስታወሰው ፖሊስ÷ የከተማዋን ሰላምና ደህንነት ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችን ህገ-ወጥ ተግባር በማጋለጥ ህብረተሰቡ ለፀጥታ አካላት እያደረገ ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!