በአዲስ አበባ ከተማ ከ90 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባ የአምቡላንስ ማቆሚያና ማሰማሪያ ጣቢያ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።
የጤና ሚኒስትር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በከተማዋ እንዲሁም በአገሪቷ ያለውን የጤና ሥርዓት ለማሻሻል የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ መሆኑን ገልጿል።
ከዚህም አንዱ የሆነው የድንገተኛ አደጋንና ፅኑ ሕክምና አገልግሎትን ማሻሻል ሲሆን በዚህም ውስጥ የቅድመ ሆስፒታል አገልግሎት ዋና መሆኑ ነው የተጠቀሰው።
ይህንንም አገልግሎት ለማጠናከር ሚኒስቴሩ ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ጋር በመሆን የቅድመ ሆስፒታል አገልግሎትን ለማሻሻል የሚያስችለውን አገልግሎት አስጀምሯል።
በቱሉ ዲምቱ ጤና ጣቢያ የተገነባው የአምቡላንስ ማቆሚያና ማሰማሪያ ጣቢያ እንዲሁም የውስጥ ዲዛይናቸው የተስተካከሉ አምቡላንሶች በይፋ ተመርቆ ወደ ሥራ ገብቷል።
ፕሮጀክቱን ከ90 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ እንደተደረገበትና ለማጠናቀቅ 1 ዓመት መፍጀቱ ተገልጿል።
የጤና ሚንስቴር ሚንስትር ደኤታው ዶክተር አየለ ተሾመ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ የቅድመ ሕክምና አገልግሎት ከቤት የማይጀምር ከሆነ በሆስፒታሎች ላይ ጫና ይፈጥራል።
በመሆኑም የቅድመ ሆስፒታል ሥራዎች ለጤና ሥርዓቱ የሚያበረክተው አስተዋጽዖ ከፍተኛ በመሆኑ በቀጣይም ለቅድመ ሕክምና ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሀንስ ጫላ በበኩላቸው መሰል ማሰማሪያና ማቆሚያ ጣቢያዎች በሁሉም ክፍለ ከተሞች እንደሚገነቡ ተናግረዋል።
ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተዉ ጣቢያዎቹ ተገንብተው ሲጠናቀቁ ለከተማዋና በከተማዋ ዙሪያ ላሉ አካባቢዎች አገልግሎት የሚሰጡ ይሆናል ።
የ20 አምቡላሶችን የውስጥ ዲዛይናቸውን በማስተካከልና በአስፈላጊው የሕክምና ግብዓት በማሟላት ደረጃቸውን ያሳደገው ደግሞ ጠብታ አምቡላንስ ነው።
በአምቡላንሶቹ ከ139 በላይ የሚሆኑ ለቅድመ ሆስፒታል ህክምና አገልግሎት የሚውሉ መሳሪያዎች ተሟልተዋል።