የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ “የላቀ ገቢ ለከተማችን ብልጽግና” በሚል መሪ ቃል የግብር ግዴታቸው በአግባቡ ለተወጡ ታክስ ከፋዮች የእውቅና እና ሽልማት አበርክቷል።
በኘሮግራሙ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ ቢሮው ላስመዘገበው የላቀ ውጤት የግብር ከፋዮች ታማኝነት፣ ሀገር ወዳድነትና አርቆ አሳቢነት ሚናው ከፍተኛ ነበር ብለዋል።
ግብር ከፋዮች ሃላፊነታቸው ብዙ ነው ያሉት አቶ ጃንጥራር፥ በፈጠራቸው የሀገርን እድገት ያፋጥናሉ፤ በሚከፍሉት ግብርም መንግስት ለሚሰራቸው ልማቶች ተኪ የለሽ ሚና ይወጣሉ በማለት አብራርተዋል።
የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ሃላፊ አቶ ሙሉጌታ ተፈራ በበኩላቸው ግብር ከፋዩ ሃላፊነቱን በሚገባ ተወጥቶ ለሽልማት መብቃት ትልቅ ድል ነው ብለዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ ግብር ከፋዮቹ በደረጃ የብር፣ የወርቅና የፕላቲኒየም ተሸላሚዎች ሆነዋል::