ሦስተኛ ቀኑን የያዘው የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ በሁሉም ክፍለ ከተሞች የ2014 ዓ.ም የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት፣ የ2015 ዓ.ም እቅድ እና እንዲሁም በወቅታዊ ሀገራዊ የሰላምና ፀጥታ ጉዳይ ላይ ውይይት ማድረጉን ቀጥሏል
በዛሬው የመድረክ ውሎ በአራዳ፣በአዲስ ከተማና በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተምች የ2014 እቅድ አፈፃፀምና የ2015 እቅድ እንዲሁም በሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ውይይቱ ቀጥሎ ውሏል፡፡
በእነዚህ መድረኮች ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ሀላፊ ዶክተር ቀንዓ ያደታ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ፅ/ቤት የመልካም አስተዳደርና የአቤቱታ ዘርፍ አማካሪ አቶ ግርማ ቤካ፤የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ም/የቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ ፤ የየ ክፍለ ከተሞች ሥራ አስፈፃሚዎች፤የሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ፅ/ቤት ኃላፊዎች፤የየ ክፍለ ከተሞቹ የካቢኔ አባላት፤የሐይማኖት አባቶች፤የሃገር ሽማግሌዎች፤አባገዳዎች፤ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችና ሌሎችም የኅብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል፡፡
በአራዳው ክፍለ ከተማ የውይይት መድረክ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ሀላፊ ዶክተር ቀንዓ ያደታ በዚህን ወቅት ባደረጉት ንግግር “በመጪው አዲስ አመትም ከምንጊዜውም በላይ ሁላችንም ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር ተቆራኝተን መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
እንዲሁም በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በተካሄደው የህዝብ ውይይት ላይ የተገኙት ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ም/ል ኃላፊ በበኩላቸው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በከተማ ደረጃ ከፀጥታ ኃይሉ በተጨማሪ ህዝባዊ አደረጃጀቶችን በማደራጀትና ወደ ስራ በማስገባት በሁሉም ረገድ ለውጦች መመዝገብ መቻላቸውን ጠቁመው በአሁኑ ጊዜም አሸባሪው የህወሓት ቡድን ለ3ኛ ጊዜ አገር ለማፈራረስ የጀመረውን ወረራ በአንድነት መመከት ይገባል ብለዋል።
በመጨረሻም በሶስቱም መድረኮች ላይ የተገኙት የስብሰባው ተሳታፊዎች በቀረበው ሪፖርት በአሰራር ረገድ የታዩ ክፍተቶችን በመሙላት ቀጣዩን የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ ወደ ላቀ የአፈፃፀም ደረጃ ለማሸጋገር ከመንግሥት ጋር በመቀራረብ እንደሚሰሩና ኢትዮጵያ ሀገራችን በማንኛውም ፅንፈኛ ሀይል እንደማትፈርስ፤ በግንባር ላይ መስዕዋት እየከፈሉልን ላሉ ህዝባዊና መከላከያ ሰራዊት ድጋፍና ደጀንነታችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
የውይይት መድረኩ በነገው ዕለትም ውይይቱ ባለተካሄደባቸው በንፋስልክ ላፍቶና በለሚ ኩራ ክ/ከተሞች እንደሚካሄድ ለማወቅ ተችሏል፡፡