የከተማ አስተዳደሩ በመጪው የክረምት ወራት በሚከናወነው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሀ ግብር 570 ሺ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ማቀዱ ለሚዲያ አካላት በሰጠው መግለጫ ይፋ አድርጓል
መግለጫውን የሰጡት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሕብረተሰብ ተሳትፎና የበጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አስፋው ተክሌ እንደተናገሩት የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ክቡር ጠቅላይ ሚንስትሩ በሰጡት አቅጣጫ መሠረት ሰው ተኮር ተግባራቶችን በልዩ ሁኔታ ለመምራት እንዲያስችል ተደርጎ እቅድ ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡
የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ በሰባት ዋና ዋና ተግባራትና በ14 ንዑሳን ተግባራት ተከፋፍሎ እንደሚከናወን የተገለፀ ሲሆን በዚህም መሰረት ለ3,400 አረጋውያን ፣ አቅመ ደካሞች፣ የአካል ጉዳተኞች ፣ የሀገር ባለውለታዎችና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተስብ ክፍሎች በመለየት የቤት እድሳት ማከናወን፤መጪውን አዲስ ዓመት፣ የመስቀል በዓል ፣ ዓረፋና ኢሬቻ በዓላትን ምክንያት በማድረግ ለ294,800 ድጋፍ ለሚሹ የህበረተሰብ ክፍሎች በከተማ አስተዳደሩ አስተባባሪነት የማዕድ ማጋራት ፤ በአርንጓዴ አሻራ መርሀግብር ላይ 1ሚሊየን የተለያዩ በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ የአካባቢ ጽዳት፤ማስዋብና ቋሚ እንክብካቤ ፤የማጠናከርያ ትምህርትና ስልጠና መርሃ ግብር፤በንቅናቄና ግንዛቤ መርሃ-ግብር በአብርሆት ናማረሚያ ቤቶች ለሚገኙ ታራሚዎች መፅሃፍ ልገሳ፤የፀረ ሱስ ንቅናቄ፤በጎነት ለሰላም የእግር ጉዞና ፓናል ውይይት፤ለ20 ሺ ዜጎች ነፃ ህክምና ፤ ደም ልገሳ መርሃግብር ፤ድንበር የለሽ የበጎ ፍቃድ ተግባራት መካተታቸውን ገልፀዋል፡፡
በክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 1.5ሚሊየን በጎ ፈቃደኞችን፤በታቀዱ ተግባራት ሁሉ ላይ በማሳተፍ የከተማችንን ልማትና እድገት ለማፋጠንና የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት ውስጥ በጎ ፈቃደኞች ጊዜያቸውን፣ እውቀታቸውን፣ ገንዘባቸውን እና ጉልበታቸውን እንዲያበረክቱ በማስቻል 570ሺ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ብሎም 2.7 ቢሊየን ብር የመንግስት ወጪን ለማዳን ከተማ አስተዳደሩ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን ሁሉም ሰው ሁሉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ አካል እንዲሆንም ጥሪ ተደርጓል ።