የአዲስ አበባ ምክር ቤት የህዝቡን ውክልና ስራዎችና አስፈፃሚውን የመከታተልና የመቆጣጠር (Check and Balance) በአግባቡ መስራት እንዲያስችለው የቋሚ ኮሙቴዎችን አደራጅቶ ወደ ስራ መግባቱ ይታወቃል፡፡
በመሆኑም የምክር ቤቱ አስፈፃሚውን የመከታተልና መቆጣጠር ስልጣን ተግባራዊ ለማድረግ ብሎም የተጠያቂነትን ስርዓት ለማስፈን ይረዳ ዘንድ በምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎችና በአስፈፃሚው አካላት (የቢሮ ሃላፊዎች ) መሃከል የተቋማቱን እቅድ መሰረት ያደረገ የስምምነት ፊርማ ከንቲባ ወ.ሮ አዳነች አቤቤ እና የአዲስ አበባ ምክር ቤት አፈጉባኤ ወ/ሮ ቡዜና አልቃድር በተገኙበት ተካሂዷል፡፡
ይህ በዛሬው ዕለት የተቋማት ሀላፊዎች እና አስፈጻሚ አካላት ጋር ያደረጉት የፊርማ ስነስርዓት ቀዳሚ ዓላማ ስራን ቀጥሮ ሰጥቶ ቆጥሮ የመረከብ አሠራር ስርዓትን ተግባራዊ የሚድረግ ፣ ፣ ምን ተግባር መቼ እና በምን ያህል በጀት እንደሚከናወን ቀድሞ አውቆ ክትትል ለማድረግና ሪፖርት ለመጠየቅ የሚያመች እንዲሁም ለአስፈጻሚው ምክር ቤት አባል ልክ እንደ ማንቂያ ደወል ሆኖ የሚያገለግል ነው ተብሏል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በፊርማው ስነስርዓት ላይ እንደተናገሩት ዛሬ ያደረግነው ስምምነት ለይስሙላ የሚደረግ ሳይሆን አስፈጻሚውን አካል ለመቆጣጠር የሚያስችል ዓላማ ያነገባና ስራን በተገቢው መንገድ ለማከናወን የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
ምክር ቤቱና ሕዝባችን የጣለብንን ኃላፊነት በተሟላ እንድንፈጽም የሚያስችል የተጠያቂነት ስርዓትን ከንግግር ባለፈ መሬት ላይ ለማውረድ የሚረዳ ፤ የተሻለ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ እንድናቀርብ የሚያስችለንም ነው ብለዋል፡፡
ዛሬ በተፈረመው ስምምነት መሰረት ህዝብ ተወካዮች አስፈፃሚውን በየጊዜው በመከታተልና በመደገፍ የከተማዋን እድገት ፤የህዝቡን ተጠቃሚነት ከፍ ለማድረግ ሊሰሩ እንደሚገባ ተነግሯል፡፡