ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሶማሌ ክልል በመገኘት የ2015 ዓ.ም አገር አቀፍ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በይፋ አስጀምረዋል።
በመርሃ ግብሩም የክልል ርእሳነ መስተዳድሮችን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተሳትፈዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው የስንዴ ልማቱ መንግስት በተለይ በከተሞች ያለውን የኑሮ ውድነት ለማሻሻል እያከናወነ ያለውን ጥረት በመደገፍ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።
ይህም ኢትዮጵያን ከራሷ አልፎ ለሌሎች እንድትተርፍ በማድረግ አዲስ ምእራፍ ይከፍታል ብለዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ በ2014 ዓ.ም የመኸር ወቅትን ሳይጨምር በበጋ መስኖ ልማት ብቻ 25 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ማምረት መቻሏ የተጠቀሰ ሲሆን፤ በዘንድሮው ዓመትም 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመስኖ በማልማት 52 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ እቅድ መያዙ ተጠቁሟል።
በመርሃ ግብሩ የተገኙት የክልል ርእሳነ መስተዳደሮች እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ በስንዴ ልማት ከፍተኛ እምርታ አስመዝግባለች።
ይህም በሁሉም መስክ በትብብርና ቁርጠኝነት መስራት ከተቻለ ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደምትለወጥ ትምህርት የሰጠ ነው ብለዋል።
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በስንዴ ልማት የተመዘገበው ስኬት እስካሁን ባለው ሂደት ለስንዴ ግዢ የሚወጣን በርካታ የውጭ ምንዛሬ እንዲቀር አድርጓል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ከውጭ ስንዴ ማስገባት ታቆማለች የሚለው እሳቤ ህልም ይመስል ነበር፤ ነገር ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ ይህን እውን ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
በቀጣይ ደግሞ ኢትዮጵያ ስንዴን ከራሷ አልፎ ለሌሎች አገራት ማቅረብ እንደምትጀምር ጠቅሰው፤ አሁናዊ ሁኔታዎች ይህን እንደሚያረጋግጡ አብራርተዋል።
በተመሳሳይ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በስንዴ ምርት የተመዘገበው ስኬት ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ምርታማነቷን በማሳደግ ከድህነት መውጣት እንደምትችል በግልጽ እንደሚያመላክት አብራርተዋል።
የአፋር ክልል ርእሰ መስተዳደር አቶ አውል አርባ የስንዴ ልማቱ በተለይ ድርቅ በተደጋጋሚ በሚያጠቃቸው እንደ አፋርና ሶማሌ ባሉ ክልሎች በስፋት እየተመረተ መሆኑ ደግሞ ለዜጎች ተሰፋ የሰነቀ ነው ብለዋል።
በሶማሌ ክልል የተመረተው ስንዴ ለሌች ክልሎችም አብነት ስለመሆኑ በመጥቀስ።
የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ርእሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳው የስንዴ ልምቱ በምግብ ራስን ከመቻል ባሻገር የአገር ሉዓላዊነትና ነጻነትን የማስጠበቂያ መንገድ መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን ህልውና ለማስጠበቅ በአውደ ውጊያ የተገኘውን ድል በኢኮኖሚው መክ በመድገም ሙሉ መድረግ ይገባል፤አሁኑ በዚህ ረገድ የስንዴ ልማቱ መልካም አብነት ነው ብለዋል።