የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙልጌታ ተፈራ በዘንድሮው በበጀት አመት የገቢ አሰባሰብ እና የሀምሌ ወር የግብር አከፋፈል ሂደትን በተመለከተ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ቢሮው በበጀት ዓመቱ በ2013 በጀት ዓመት ለመሰብሰብ ያቀደውን 42 ቢሊየን 479 ሚሊየን ብር ሙሉ በሙሉ ገቢ ማሰብሰቡን የገለጹት አቶ ሙሉጌታ ከባለፈው አመት ገቢ ቻር ሲነጻጸር በ6.8 ቢሊየን ብር ብልጫ እንዳለለው ተናግረዋል።
በ2014 የበጀት አመትም 48 ቢሊየን 572 ብር ገቢ ለመሰብሰብ እቅድ መያዙን እና በሚቀጥሉት አራት ወራትም ከ20 ቢሊየን ብር በላይ ግብር ለመሰብሰብ እንደሚሰራ የቢሮ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
ከነገ ሐምሌ 1 ቀን ጀምሮ የ2014 የግብር ማሳወቂያ እና መክፈያ ለማስጀመር የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን እና የግብር አከፋፈል ስርዓቱን ፈጣንና ቀልጣፋ እንዲሆን ዘመናዊ አሰራር መዘርጋቱን ተናግረዋል፡፡
በዚሁ መሰረት በ2014 በጀት ዓመት የደረጃ ‘ሐ’ ግብር ካፋዮች የግብር መክፈያ ጊዜ ከሐምሌ 1 እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2013 ሲሆን የደረጃ ‘ለ’ ግብር ከፋዮች ግብር መክፊያ ጊዜ ከሐምሌ 1 እስከ ጳጉሜ 5 ቀን 2013 ዓ.ም ይሆናል እንደሚሆን አቶ ሙሉጌታ ጠቁመዋል፡፡
የደረጃ ‘ሀ’ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ደግሞ ከሐምሌ 1 እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2014 እንደሚሆን ገልጸው ሁሉም ግብር ከፋዮች በተቀመጠላቸው መርሐግብር ክፍያቸውን እንዲከፍሉ አሳስበዋል፡፡