በቡድን በመደራጀት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ንብረት የሆነ ከ7መቶ ሺህ ብር በላይ የዋጋ ግምት ያለው የኤሌክትሪክ ገመድ በመስረቅ በተሽከርካሪ ጭነው ለማምለጥ የሞከሩ 8 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገለፀ፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ወንጀሉን የፈፀሙት በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ልዩ ቦታው አጃምባ ኮንዶሚኒየም ሳይት ውስጥ ነው፡፡ ግለሰቦቹ በለሊቱ ክፍለ ጊዜ ጭለማን ተገን በማድረግና በቡድን ተደራጅተው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ንብረት የሆነ 7 መቶ 28 ሺህ ብር የዋጋ ግምት ያለውን 616 ጥቅል የኤሌክትሪክ ገመድ የመጋዘኑን በር ሰብረው ከሰረቁ በኋላ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ-3-10402 ኦሮ በሆነ አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪ ጭነው ለማምለጥ ሲሞክሩ በወቅቱ በስራ ላይ የነበሩ የፖሊስ አባላት ከመስሪያ ቤቱ የጥበቃ ሰራተኞች እና ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በመተባበር ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት የተሰረቀውን ንብረት ጨምሮ 8 ግለሰቦች ከእነተሽከርካሪው በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው መሆኑን የአዲስ ፖሊስ አስታውቋል፡፡