ጌታሁን አስፋው ጌታሁን የተባለ እና በአማራ ክልል የህዝብ ሰላም እና ጸጥታን ለሚያውኩ ጽንፈኛ ሀይሎች የሎጀስቲክስ አቅራቢ እንደሆነ የተጠረጠረ ግለሰብ በክፍለ ከተማው ወረዳ ሁለት የሚገኝ ቤትን በመከራየት የተለያዩ ወታደራዊ ቁሰቁሶችን በማከማቸት ለጽንፈኛ ቡድኖቹ ለማቅረብ በመንቀሳቀስ ላይ እያለ በጸጥታ ሀይሎች ክትትል ሊደረስበት ችሏል፡፡
የመከላከያ መረጃ ዋና መምሪያ፣ የአዲስ አበባ ከተማ የጸጥታ ዘርፍ ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ እና የፌደራል ፖሊስ በጋራ ባካሄዱት ኦፕሬሽን ግለሰቡ ከተከራየው ቤት የጦር መሳሪያዎች እና ጥይቶች፣ የመካከለኛ እና የረጅም ርቀት ወታደራዊ የመገናኛ መሳሪያዎች ፣ ልዩ ልዩ ትጥቆች እና ወታደራዊ አልባሳት፣ የተለያዩ ሰነዶች እና ጽንፈኛ ሀይሎቹ የሚጠቀሙባቸው ልዩ ልዩ ቁሳቁሶች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
ከመከላከያ ሰራዊት እና ሌሎች የጸጥታ አካላት ውጭ በግለሰቦች እጅ ሊኖር የማይገባ የከፍተኛ ርቀት ወታደራዊ የመገናኛ መሳሪያም በቁጥጥር ስር ከዋሉ ቁሳቁሶች መካከል የሚገኝበት እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡
ተጠርጣሪው ግለሰብ የተለያዩ ስሞችን በመጠቀም መታወቂያዎችን በማውጣት ሲንቀሳቀስ የነበረ ሲሆን ከአማራ ክልል በመሰወር በአዲስ አበባ ከተማ የግለሰብ ቤት በመከራየት ለጽንፈኛ ሀይሎች ሎጀስቲክስ ሲያሰባስብ እና ስልጠናዎችንም ሲሰጥ ቆይቷል፡፡
ግለሰቡን በቁጥጥር ስር ለማዋል የተቀናጀ ክትትል እየተደረገ እና ተጨማሪ ምርመራም እየተካሄደ የሚገኝ ሲሆን ህብረተሰቡም መሰል የህዝብ እና የሀገርን ሰላም እና ጸጥታ ለማወክ የሚንቀሳቀሱ ሀይሎችን ሲያገኝ ለጸጥታ አካላት ጥቆማ በመስጠት የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግ ጥሪ ቀርቧል፡፡